AMN – ታኅሣሥ 20/2017 ዓ.ም
ባለፉት የለውጥ አመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እውን ያደረጉ ስኬቶች መመዝገባቸውን የብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሯ በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት የለውጥ አመታት ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ህጻናት፣ አረጋውያን እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ተከናውነዋል።
ከሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት አንጻርም መንግስት በጉልህ የሴቶች ተሳትፎን ያረጋገጡ ስራዎች መስራቱን ገልጸው፤ በተለይም በፖለቲካው ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል በርካታ ሴት አመራሮችን ማፍራት መቻሉን ተናግረዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍም በተለያዩ መስኮች በማደራጀት ራሳቸውን ብሎም ሀገርን በሚጠቅሙ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ መደረጉን ጠቁመዋል።
ሚኒስትሯ እንደገለጹት በህጻናት ላይ በተሰራው ስራ ባለፉት የለውጥ አመታት ከ500 ሺህ በላይ ህጻናት በተለያዩ የማህበራዊ አማራጭ ድጋፎችን እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
እንዲሁም ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ያደረጉ ህጻናትን ወደ ማእከል በማስገባት ከቤተሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ዘላቂ የሆነ ስራ በመስራት ተመልሰው ወደ ጎዳና የማይወጡበትን ሁኔታ መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።
ወጣቶች በፖለቲካ፣ ማህበራዊ እንዲሁም በኢኮኖሚው ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልጸዋል።
ወጣቶች በራሳቸው እንዲደራጁ ከማድረግ አኳያ የኢትዮጵያ ወጣቶች ካውንስል እንዲመሰረት መደረጉን ጠቁመው አሁን ላይ በተለያዩ ክልሎች እየተቋቋመ መሆኑንም ገልጸዋል።
ካውንስሉ እስካሁን በስድስት ክልሎች መቋቋሙን በማከል።
እንዲሁም በኢኮኖሚው ዘርፍ በማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም በመንግስት በተቀረጹ የተለያዩ ኢኒሼቲቮች ላይ ወጣቶች እንዲሰማሩ መደረጉን ጠቁመዋል።
በዚህም በወጣቶች ላይ የተሰራው ስራ ውጤት እየተመዘገበበት እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡