AMN – ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ታሪክ መማረሪያ ሳይሆን መማሪያ፤ የክት ሳይሆን የአዘቦት መሆን አለበት ብለዋል፡፡
ዛሬ ከምሁራን፣ ከኪነ ጥበብ፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ አባላት እና ከታዋቂ ሰዎች ጋር ታሪካዊ ዕሴቱን ጠብቆ በታደሰው የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ሙዝየም ተገናኝተናልም ብለዋል አቶ ተመስገን፡፡
ይህ ሙዝየም ሕዝብ የሀብቱ የሩቅ ተመልካች ሳይሆን ተጠቃሚ መሆን አለበት በሚል መርሕ ተፈጥሯዊ ሀብቶቻችንን አውቀን፤ ዕሴት ጨምረን ወደ ሀብትነት የመቀየር ጉዟችን አንድ ማሳያ ነውም ብለዋል፡፡
የታሪክና የቅርስ ምሁራን ደግሞ ታሪካችን እና ቅርሳችን ለሕዝቦች መቀራረብና መተሣሠር እንዲጠቅም ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
አሳዛኝና አስቀያሚ ታሪክ የሌለው ሀገር የለም፡፡ ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘባችንን ማዋል ያለብን ደግሞ ሕዝብን የሚያቀራርቡ፣ የሚያኮሩ እና የሚያስተሣሥሩ ታሪኮቻችን ላይ ነው፡፡
የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችም ይሄ ሙዝየም የድርሰታችሁ፣ የግጥማችሁ፣ የፊልማችሁ፣ የዜማችሁ ማዕከል እንደሚሆን አምናለሁ፡፡
ፊልሞቻችሁና፣ ሙዚቃዎቻችሁ፤ ድርሰቶቻቸሁና ቅኔዎቻቸሁ ደግሞ እነዚህን የኢትዮጵያ ከፍታ ማሳያ ሥፍራዎች እንዲዳስሱ አደራ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡
የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ቅርሶቻችንንና ታሪካዊ ቦታዎቻችንን ስናለማ እያደረጋችሁ ላላችሁት እገዛ እያመሰገንሁ ይሄ እገዛችሁ እንዲቀጥል አደራ እላለሁ ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው፡፡