አምራች ኢንዱስትሪውን ከመደገፍ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጤታማ ተግባር በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡
ከ250 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉበት “ከሸማችነት ወደ አምራችነት” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያ -አዲስ አበባ ታምርት የ2017 ዓ.ም የአምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይ በዛሬው እለት ተከፍቷል::
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አምራች ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያመጣ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ዘርፍ ገቢ ምርትን በመተካት፣ ኤክስፖርትን በማሳደግ፣ የስራ እድልን በመፍጠርና ተወዳዳሪ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ውጤታማ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ዘርፉን በመደገፍ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጤታማ ተግባር በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል::
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው አዲስ አበባ ከያዘቻቸው የልማት እቅዶች መካከል ለአምራች ኢንዱስትሪው ትኩረት በመስጠት፤ ዘርፉ ለኢኮኖሚው እድገት የሚያደርገውን አስተዋፅኦ በማሳደግ ለአምራቾች መሰረት ልማት በማሟላት፣ የፋይናንስና ማሽነሪ አቅርቦት በማሳደግ እንዲሁም ማስፋፊያ ቦታዎችን በመስጠት የማያቋርጥ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ- አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት ሶስት አመታት ሲካሄድ አመርቂ ውጤት ተገኝቶበታል ያሉት ምክትል ከንቲባው የዘንድሮው የኢትዮጵያ – አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄም ከባለፈው በቂ ልምድ የተወሰደበት እና በአይነቱም የተለየ መሆኑንም ገልጸዋል::
በዚህ የኢትዮጵያ- አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መሳተፋቸዉን ከአዲስ አበባ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል፡፡