AMN – የካቲት 8/2017 ዓ.ም
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፓን አፍሪካኒዝም መገኛ እና የአፍሪካ ሕብረት የኩራት ምንጭ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ እንኳን በሠላም መጣችሁ ሲሉ ለመሪዎቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
እጅግ ተለዋዋጭ እና በርካታ ፈተናዎች በተሞላችው ዓለም ውስጥ፣ እርግጠኛ መሆን በማይቻል እና በዕድሎች መካከል ባለ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንገኛለን ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ወቅቱ አንድነታችንን እና ጥንካሬያችንን የሚጠይቅ ሆኗል ብለዋል፡፡
“የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያን እና ለዘርዓ አፍሪካውያን” የሚለው የዘንድሮው ጉባኤ መሪ ቃል የአህጉሪቱን ዕድገት የገታውን እና ለዘመናትን የተካሄደውን ታሪካዊ ኢ-ፍትሀዊነት እና ድራማ እንዲያበቃ የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
“የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያን እና ለዘርዓ አፍሪካውያን” የሚለው የዘንድሮው የጉባኤው መሪ ቃል ምፅዋት ወይም የፋይናንስ ድጋፍን የመፈለግ ሳይሆን የፍትሀዊነት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የማካካሻ ጥሪው የሚሊዮኖችን ክብር መጠበቅ፣ ድህነትን ማጥፋት፣ እኩልነትን ማስፈን እንዲሁም ዘረኝነት እና ኢፍትሀዊነትን መከላከልን ያካትታል ብለዋል፡፡
‘ይህ ብቻም አይደልም ሀብቶቻችንን መውሰድ፣ በማደግ እድሎቻችን ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ማስቆምን ይጠይቃል’ ሲሉ አክለዋል፡፡
‘የማካካሻ ጥሪያችን ከቃል ያለፈ እና ጠንካራ ተግባርን የሚፈልግ ነው’ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁሉንም የሰው ልጅ ክብር ያገናዘበ እና በአህጉራችን ላይ ለደረሰው ጉዳት እውቅና የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
ዘላቂ ሠላም፣ ፍትህና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ከጂኦፖለቲካዊ ውጥረት እና በቅኝ ገዥዎች ከተጫነው መከፋፈል መውጣት ይኖርብናል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ግጭት አፈታት፣ ዲፕሎማሲ እና የሠላም ግንባታችን ሥራ በእኛው ጠንካራ ጥረት ሊሳኩ ይገባል፡፡ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርህ በመመራትም ሠላምና መረጋጋትን ማምጣት እንችላልን ብለዋል፡
በፖለቲካ፣ ሳይንስ፣ በኢኮኖሚ እና በኪነጥበብ ረገድ ያሳካናቸው ሥራዎችም ሊደነቁ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ስትራቴጂካዊ የሆነው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና በሀገራት መካከል የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎችን የሚያበረታታ እና በውጭ ሀገራት ላይ ያለውን ጥገኝነት የሚቀንስ እንዲሁም እራስን ለመቻል የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በማሬ ቀጦ