የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል-ትምህርት ቢሮ

You are currently viewing የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል-ትምህርት ቢሮ

AMN – ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም

በትምህርት ቤቶች የተጀመረው የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊዎች ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ኤፍኤም 96.3 ሬዲዮ “አገልጋዩ” ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ ከተማ አስተዳደሩ ሪፎርም እየሰራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች መካከል የትምህርቱ ዘርፍ አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

የትምህርት ሪፎርሙ ካካተታቸው መካከል የተሻለ ትምህርት ለትውልድ በሚል መነሻ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ዋነኛው መሆኑም ተገልጿል፡፡

በዚህም በርካታ ትምህርት ቤቶች ከዝቅተኛ ተነስተው ከፍተኛ ደረጃ ውስጥ መግባታቸውን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዲናኦል ጫላ ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ማሰባሰብ መቻሉን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው በዚህም 246 ትምህርት ቤቶች ዕድሳት ተደርጎላቸው ለመማር ማስተማር ምቹ እንዲሆኑ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም 280 ትምህርት ቤቶች ላይ ማስፋፍያ በማከናወን ተጨማሪ ክፍሎች መገንባታቸው የተገለጸ ሲሆን 573 ትምህርት ቤቶች ደግሞ የመማርያ ክፍሎቻቸው ጥራታቸውን እንዲጠብቁ መደረጉን አውስተዋል፡፡

ይህም ለትውልዱ የተሻለ ትምህርትን ለማድረስ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡

በኤፍ ኤም 96.3 ሬዲዮ አገልጋዩ ፕሮግራም ላይ እንግዳ የነበሩት የቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ከማል በበኩላቸው፤ በትምህርት ቤቶች ደረጃ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ ተማሪዎች የትምህርት ፍቅር እንዲያድርባቸው እና ውጤታቸውም ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንዳስቻለ ገልጸዋል፡፡

በየሺዋስ ዋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review