የኢትዮጵያ እና ጂቡቲ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለጎረቤት አገራት ትስስር እንደምሳሌ የሚነሳ ነው፡-ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

You are currently viewing የኢትዮጵያ እና ጂቡቲ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለጎረቤት አገራት ትስስር እንደምሳሌ የሚነሳ ነው፡-ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

AMN – ታኅሣሥ 20/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ እና ጂቡቲ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለጎረቤት አገራት ትስስር እንደምሳሌ የሚነሳ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ ከጂቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃሙድ አሊ የሱፍ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርጓል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሁለቱ ወንድማማች አገራት መካከል ያለው የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለጎረቤት አገራት ትስስር እንደምሳሌ የሚነሳ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ያበረከተችውን አስተዋጾ በመጥቀስ፣ አሁንም አልሸባብን ለመዋጋት ያላትን ቁርጠኛነት ገልጸዋል።

ልዑካኑ በጂቡቲ የሚሰጠውን የወደብ አገልግሎት ይበልጥ ለማቀላጠፍ፣ የነዳጅ ተርሚናል አቅም ለመጨመር፣ የዲኪል-ጋላፊ መንገድ ግንባታ የማጠናቀቅ ሂደት፣ የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች እና አጠቃላይ የገቢ-ወጪ ምርት ዝውውር ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል።

የጂቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃሙድ አሊ የሱፍ በበኩላቸው በ ሁለቱ አገራት መካከል ያለው ወዳጅነት በሁለቱ አገራት ህዝቦች ቤተሰባዊነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ጂቡቲ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ማስፈን ላይ እየሰራች ያለችው ስራ በማመስገን፣ አልሸባብን መከላከል ላይ በጋራ እንደምትሰራ ገልጸዋል።

ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያን የነዳጅ ፍላጎት ባማከለ መልኩ የነዳጅ መስመር ከደመርጆግ ወደብ ጋር በማያያዝ ተጨማሪ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ የዲኪል-ጋላፊ የመንገድ ስራም በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review