AMN – ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም
ከተማችን አስተማማኝ ሠላሟ ተረጋግጦ ዘላቂ ልማት ማስመዝገብ የቻለችው ከማህበረሰቡ ጋር የተሳሰረ ጠንካራ የጸጥታ ስራ ስለተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ አስታወቁ።
የአዲስ አበባ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ መጪውን የጥምቀት በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በደመቀና ባማረ መልኩ ለማክበር በከተማዋ ከሚገኙ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከፓርኪንግ አገልግሎት ሰጪ ማህበራት እና ከታክሲ ተራ አስከባሪ ወጣቶች ጋር ግምገማዊ ስልጠና አካሂዷል።
በግምገማዊ ስልጠናው ላይ የአዲስ አበባ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እንደገለፁት በመዲናዋ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉት የወንጀል ድርጊቶች የማህበረሰቡ የስጋት ምንጭ መሆናቸውን ጠቁመው በሂደት ለማህበረሰቡ የስጋት ምንጭ በማይሆኑበት ደረጃ ማድረስ ይኖርብናል ብለዋል።
በከተማዋ የሚሰሩ የታክሲ ተራ አስከባሪዎችና የፓርኪንግ አገልግሎት ማህበራት ለህብረተሰቡ ጸጥታ አጋዥ በሚሆኑበት አግባብ እንዲሠሩ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል ፡፡
ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና መንገድ አቆራርጦ በመጫን ህዝብን የሚያማርሩ የታክሲ ትራንስፖርት ሰጪዎችን ለአብነት ያነሱት ወ/ሮ ሊዲያ ተራ አስከባሪ ማህበራቱ ህግና ስርአትን ተከትለው የሚሰሩበትና ለጸጥታ አጋዥ የሚሆኑበትን አሰራር ለመዘርጋት ከትራንስፖርት ቢሮ ጋር ሆነን እንሠራለን ብለዋል።
በሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የጸጥታ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ኮማንደር ሙሉጌታ በጋሻው በታክሲ ተራ ማስከበር እና በፓርኪንግ አገልግሎት የተሠማሩ ማህበራት ዙሪያ እስካሁን ያለው አሰራር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ስለመምጣቱ ባቀረቡት ጽሁፍ ገልጸዋል።
ተራ አስከባሪዎች ከተተመነላቸው በላይ ክፍያ ከሾፌሮች መቀበል ፣ ታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶቻቸው ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ ዝም ማለት ፣ መንገድ ሲያቆራርጡ ተባባሪ መሆን ፣ ታክሲዎች ከተርሚናል ውጪ ሲጭኑ እና መጫን ከሚገባቸው የተሳፋሪ ቁጥር በላይ ሲጭኑ አለመከልከልና ሳይደራጁ በየቦታው የተራ አስከባሪነት ገንዘብ መቀበልን የመሳሰሉ ህገወጥ ተግባራት እንደሚከናወኑ በጥናት መለየቱንም አመልክተዋል።
ስለሆነም ይህንን አሠራር ወደ ህጋዊ መስመር ለማምጣት በከተማዋ ትኩረት እንደተሰጠበት ጠቅሰዋል።
ለዚህም ከትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመሆን መመሪያና አሰራር እየተዘጋጀለት ስለመሆኑ ኮማንደር ሙሉጌታ አንስተዋል።
የወንጀል መከላከል ስራውን በውጤታማነት ለማከናወን ይቻል ዘንድም የትራንስፖርት ባለስልጣን ከተራ ማስከበርና ከፓርኪንግ አገልግሎት ማህበራት የጸጥታ አካላትና ትራፊክ ፖሊስ ጋር ቅንጅት ፈጥረው ሊሠሩ እንደሚገባም በግምገማዊ ስልጠናው ላይ የተሳተፉ የየማህበራቱ ተወካዮች ተናግረዋል።
በምትኩ ተሾመ