የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ዕድሳት ተደብቆ የቆየውን የኢትዮጵያ የዳበረ የዲፕሎማሲ ታሪክ ለዓለም ያሳየ ነው-አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

You are currently viewing የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ዕድሳት ተደብቆ የቆየውን የኢትዮጵያ የዳበረ የዲፕሎማሲ ታሪክ ለዓለም ያሳየ ነው-አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

AMN – ጥር 3/2017 ዓ.ም

የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ዕድሳት ተደብቆ የቆየውን የኢትዮጵያ የዳበረ የዲፕሎማሲ ታሪክ ለዓለም ገልጦ ያሳየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ፡፡

የብሔራዊ ቤተ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቅርብ ክትትል ደረጃውን ጠብቆ ታድሶ ለምርቃት በቅቷል፡፡

ዕድሳቱ የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክና ገናና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ደምቀው እንዲታዩ አድርጓል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንዳሉት፤ ብሔራዊ ቤተ መንግሥቱ በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ታሪክ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡

ከዕድሳቱ በፊት የሀገራትን መሪዎችና ዲፕልማቶችን ለማስተናገድ የማይመጥን እንዲሁም የኢትዮጵያን ገናና የዲፕሎማሲ ታሪክ ጥላሸት የሚቀባ ጎስቋላ ሥፍራ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ ኃላፊነቶች በሠሩባቸው ሁለት አስርት ዓመታት የሚያውቋቸው የቤተ መንግሥቱ ጥቂት ክፍሎች ኢትዮጵያን የማይመጥኑ እንደነበሩም አምባሳደር ብርቱካን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተሰጧት የክብር ሥጦታዎች ከዕይታ እንዲሸሸጉ ተደርገው በመቆየታቸው ገናና የዲፕሎማሲ ታሪካችንንና አቅማችንን ማሳየት ሳንችል ቆይተናል ብለዋል፡፡

ዛሬ ላይ የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ዕድሳት የትናንት የዲፕሎማሲ ክብራችንን፣የዛሬ ኩራታችንና የነገ መዳረሻችንን በመግለጥ ለህዝብ እይታ መብቃቱን ገልጸዋል፡፡

በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከአውሮፓ፣ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና ኤዥያ ሀገራት የተሰጡን የክብር ስጦታዎች በቅርስነት ለጎብኝዎች ቀርበዋል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፡፡

ለአፍሪካ ሀገራትም የታሪካቸው ማስታወሻ ሊሆናቸው ስለሚችል “የጋራ ሀብታችን ነው” የሚል ስሜት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ቤተ መንግሥቱ የኢትዮጵያን ክብር የሚመጥን እና የዲፕሎማሲ አቅሟን የሚያሳድግ የኩራት ምንጭ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review