መጽሐፍት ለትውልድ፣ በየሳምንቱ ሰኞ ዕለት ጠቃሚ ናቸው ያልናቸውን መጽሐፍት ለአንባቢ የምንጋብዝበት አምዳችን ነው።
የመጽሐፍቱ ምርጫ የእናንተ የውድ ተከታዮቻችንም ጭምር ነው፤ አንብባችሁ የወደዳችሁትን መጽሐፍ ብትጠቁሙን እኛም አንብበን ያላነበቡ እንዲያነብቡት መልሰን እንጋብዛለን።
ለዛሬ “የጥበብ ዋልታዎች”ን በጨረፍታ ዳስሰን ሙሉውን እንዲያነብቡት ጋብዘናችኋል። እነሆ!!
ርዕስ – የጥበብ ዋልታዎች
ደራሲ – ይጥና ደምሴ
የታተመበት ጊዜ – በ2011
የገጽ ብዛት – 250
መጽሐፉ በጥበብ ዙሪያ የሚያተኩር ሆኖ 14 የአገራችን የጥበብ ባለውለታዎች ተካትተውበታል። ከእነዚህን የጥበብ ሰዎች አብዛኞቹ የማይታወቁ ነገር ለሙዚቃው ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ናቸው።
እንደሚታወቀው አብዛኞቹ የአገራችን የጥበብ ባለሙያዎች የሕዝብ ፍቅር እንጂ ሀብት እንደሌላቸው ይታወቃል።
በተለይም ቀደም ብለው የነበሩት በርካቶቹ የአገራችን የጥበብ ፈርጦች ወደ መጨረሻው የሕይወት ዘመናቸው በችግር እና በመከራ ያልፋሉ። ችግር ሲገጥማቸው ሲደገፉ እና በዕርዳታ ሲታከሙ ይስተዋላል።
እናም የዚህ መጽሐፍ ዓላማ የቀደሙቱ የጥበብ ሰዎቻችን ኑሮ እና ሕይወት ባይመቻቸውም የሠሩትን ድንቅ የጥበብ ሥራ ተሞክሮ ይሆን ዘንድ ለተተኪዎቻቸው በማስተዋወቅ እነዚህ የጥበብ ሰዎች ከየት ተነሥተው የት እንደደረሱ የሕይወት ተሞክሯቸውን ማጋራት ነው።
በመጽሐፉ የ14ቱ የጥበብ ሰዎች ታሪክ አጠር ባለ መንገድም የቀረበበት ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በሕይወት ያሉም የሌሉም ተካትተውበታል።
ከእነዚህ የጥበብ ሰዎች አንዳንዶቹ ለአገራችን የሙዚቃ ዕድገት ጉልህ አሻራቸውን ያሳረፉ ቢሆንም ያልተዘመረላቸው እና ፈጽሞ የማይታወቁ መሆናቸው አስገራሚ ያደርገዋል።
አንዳንዶቹን ጠቀስ ብናደርግ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ እነ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠን ያበቁ እና ለሌሎች በርካታ ድምፃዊያን በርካታ ግጥም ያበረከቱ የጥበብ ሰው እንደሆኑ ይገለጻል።
እኚህ ሰው ደሞዛቸውን እንኳ በሽልማት የሚጨርሱ ስለመሆናቸው ይነገራል። በተለይም በጣም የሚያረካ እና ጥሩ የሙዚቃ ግጥም ሲሰሙ ይሸልማሉ። አሸላለማቸው ደግሞ “ከወር ደሞዜ ላይ ተቀናሽ የሚሆን ለአቶ እገሌ ይህን ያህል ብር ይሰጥልኝ” ብለው ለመሥሪያ ቤታቸው ሒሳብ ክፍል ያመለክቱ ነበር ይባላል።
እኚህ የጥበብ ሰው በተለይም ድምፃዊ ጥላሁን የተጫወተውን “የጠላሽ ይጠላ…” የሚለውን ታዋቂ ሙዚቃ ግጥም እርሳቸው እንደደረሱት ይነገራል። ነገር ግን ይህን አገርኛ ዜማ እርሳቸው ሳይሰሙት እና በእርሳቸው ጊዜ ለሕዝብ ጆሮ ሳይበቃ በሕይወት አልፈዋል። እኚህን የጥበብ ሰው ታዲያ ብዙም ሰው አያውቃቸውም።
ሌላው የመጽሐፉ ባለታሪክ አርቲስት ተስፋዬ ገብሬ ነው። ተስፋዬ በይበልጥ “ስፖርት” በሚለው ዝነኛ ሙዚቃው ይታወቃል። ነገር ግን የአርቲስት ተስፋዬ አሟሟት ለብዙዎች ግልጽ አይደለም።
መጽሐፉ ስለ አርቲስቱ አንዳንድ ነገሮችን ያትታል። የአርቲስት ተስፋዬ ገብሬ ታናሽ እህት ወ/ሮ አስካለ ገብሬ ስለ ወንድማቸው አሟሟት በተሳሳተ መንገድ የሚወራውን እርሳቸው ትክክለኛውን ነገር ለመጽሐፉ ያብራራሉ።
ወ/ሮ አስካለ ጣልያን አገር ጣልያናዊት አግብቶ ይኖር የነበረውን ወንድማቸውን አስታምማው እንደነበር እና ወንድማቸው ተስፋዬ በሕመም ምክንያት ሕይወቱ እንዳለፈ ያስረዳሉ።
ሌላው በመጽሐፉ የተጠቀሰው የጥበብ ሰው “ተንቀሳቃሹ ቴአትር ቤት” እየተባለ የሚጠራው አባተ መኩሪያ ነው። አባተ በአገራችን የቴአትር ዕድገት ውስጥ ፈር ቀዳጅ እንደሆነም በብዙዎች ዘንድ ይነገራል።
ሌላው በመጽሐፉ ከተጠቀሱት ውስጥ እምብዛም የማይታወቀው ማስረሻ ሽፈራው እና የክራሯ ንግሥት አስናቀች ወርቁ ናቸው።
እነዚህ በሙዚቃው ዓለም ትልልቅ ሥራ የሠሩ ነገር ግን የተደበቁ እና ብዙም ያልተዘመረላቸው እንዲሁም ሳይደላቸው ለጥበብ ኖረው ያለፉ የጥበብ ሰዎች ስለመሆናቸው የመጽሐፉ ደራሲ በቁጭት ይገልጻሉ።
ሌሎቹ የመጽሐፉ ባለታሪኮች ሙሴ ነርሲስ እና ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ናቸው። ሁለቱ ግለሰቦች በጋራ በመሆን የንጉሡ ዘመንን የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር እንደደረሱ ደራሲው ያነሳሉ።
ሙሴ ነርሲስ ብዙ ሙዚቀኞችን ሙዚቃ ያስተማሩ አፍቃሪ ኢትዮጵያ እንደነበሩ በመጽሐፉ ተመልክቷል። “አፍሪካ፣ አፍሪካ፣ አፍሪካ ሀገራችን…” የሚለውን ዜማ የደረሱት እሳቸው እንደነበሩ ይጠቀሳል።
ሌላው ባለታሪክ አቶ ተስፋዬ ለሜሳ ናቸው። እኚህ ሰው “የእግር ብረትን ሰብሮ ለጥበብ ስደትን የመረጠ ሁለገብ ከያኒ” ተብለዋል።
ብዙም የማይታወቁት አቶ ተስፋዬ ከልጅነታቸው ጀምሮ የጥበብ ፍቅር የነበራቸው ሰው እንደነበሩ እና ከብሔራዊ ቴአትር ቤት እንደማይጠፉ ይወሳል። ሁኔታው ያላማራቸው እና አዝማሪ ይሆንብኛል ብለው ስጋት የገባቸው የአቶ ተስፋዬ አባት በእግር ብረት እንዳሰሯው እና በኋላም አቶ ተስፋዬ የእግር ብረቱን ሰብረው ምድር ጦር ኦኬስትራ እንደተቀጠሩ ይነገራል።
ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ የተጫወታቸውን “ምንታረጊዋለሽ” እና “ፈልጌ አስፈልጌ” ሙዚቃ ግጥሞች የደረሱት አቶ ተስፋዬ ናቸው።
ሌላው የማይታወቁት የጥበብ ሰው ማስረሻ ሽፈራው ናቸው። የድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ “የቀይ ዳማ” የጥላሁንን “ይህቺ ናት ጨዋታን” እና ሌሎች በርካታ ግጥሞችን የሠሩ ቢሆንም ነገርግን በስተመጨረሻ በአስቸጋሪ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዳለፈ ይነገራል።
መጽሐፉ መታሰቢያነቱ ለሸረፈዲን ሙሳ ነው ይላሉ ደራሲው። አቶ ሸረፈዲን ጋዜጠኛ እና ገጣሚ ነበሩ። ለብዙ የጥብብ ሰዎችም ግጥም መስጠታቸው ይወሳል።
ቀሪውን ታሪክ ደግሞ እርስዎ መጽሐፉን አንብበው ለአገራችን ሙዚቃ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ነገር ግን ያልተዘመረላቸውን ዕንቁ የጥበብ ሰዎች ይተዋወቁ ዘንድ እንጋብዛለን። ቸር እንሰንብት!
በሰለሞን በቀለ