AMN – ጥር 7/2017 ዓ.ም
አሜሪካ ከብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ጋር በተያያዘ የቻይና እና የሩሲያ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው ስማርት መኪኖችን ከሀገሪቱ ገበያ የሚያግድ ደንብ አዘጋጅታለች።
ደንቡን ለማዘጋጀት ያስፈለገው ዋሽንግተን እንደ ቻይና እና ሩሲያ ባሉ ተቀናቃኞች የተደቀኑ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ የደኅንነት ስጋቶችን ለማስወገድ በማለም መሆኑ ተመላክቷል።
የአሜሪካ የንግድ ሚኒስትር ጂና ራይመንዶ፣ ዛሬ ላይ መኪኖች ብረት እና ጎማ ሳይሆኑ ኮምፒዩተሮች ናቸው ብለዋል።
ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ካሜራዎች፣ መነጋገሪያዎች፣ ዓለም አቀፍ መገኛን የመከታተያ ሥርዓት እና ሌሎች ከኢንተርኔት ጋር የተገናኙ ቴክኖሎጂዎችን የያዙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ደንቡም በቻይና እና በሩሲያ ቴክኖሎጂ የሚመረቱ ተሸከርካሪዎችን ከአሜሪካ ጎዳና ለማስወጣት ዓላማ ያደረገ እንደሆነ አንሥተዋል።
አሁን ላይ ደንቡ ተግባራዊ የሚደረገው ከ4 ሺህ 536 ኪሎ ግራም በታች በሆኑ የመንገደኞች ተሸከርካሪዎች ላይ እንደሚሆን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ዘመናዊ ከባድ የጭነት ተሸከርካሪዎችን እና አውቶቡሶችን የሚመለከት ልዩ ደንብም በቅርቡ እንደሚጸድቅ ማመላከታቸውን ዘ ኢኮኖክ ታይምስ ዘግቧል።