በኢኮኖሚ ማሻሻያው እየተጠገነ ያለው ስብራት

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ብትፈተንም ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች መቀጠሏን መንግስት ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ተቋማት በተለያየ ጊዜ ሲያወጧቸው የነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከወራት በፊት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራውን በተመለከተ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከ2010 እስከ 2015 ባሉት በጀት ዓመታት በአማካይ የሀገር ውስጥ ምርት በ7 ነጥብ 1 በመቶ፣ በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ የ8 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ተመዝግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት 20 ዓመታት ሲያድግ እንደነበር ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየት የሰጡት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት እያደጉ ካሉ ጥቂት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆና ነው የቆየችው፡፡ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በከፍተኛ መጠን አድጎ አሁን ላይ ከ200 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ደርሷል ብለዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ – አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ

ነገር ግን ይላሉ አቶ ዘመዴነህ፤ ሲመዘገብ የነበረው የኢኮኖሚ እድገት በመንግስት ከፍተኛ ወጪ በተስፋፋ የመሰረተ ልማት እድገት የመጣ፤ የግሉን ዘርፍ ያላሳተፈ በመሆኑ የሚፈለገውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት አላስቻለም፡፡ የመንግስት ወጪ በከፍተኛ ብድርና እርዳታ የተሸፈነ በመሆኑ የውጭ ዕዳ ጫና በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ እንደ የዋጋ ግሽበት፣ የወጪ ገቢ ንግድ ሚዛን አለመመጣጠን፣ ስራ አጥነት ያሉ ፈተናዎችም አጋጥመውት ቆይቷል፡፡

ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያመጣ፣ የአገልግሎት፣ ኢንዱስትሪና ግብርና ዘርፎች የሚፈለገውን ያህል ውጤት እንዲያስገኙ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባ ታምኖበት ሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ተዘጋጅቶ እየተተገበረ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አቶ ዘመዴነህ ያነሳሉ፡፡ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ባዘጋጀው የኢትዮጵያ የአስር ዓመት የልማት እቅድ ሰነድ ላይም ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በየዓመቱ እስከ 10 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት እንደታቀደ ተቀምጧል፡፡

ከዚህ ባሻገር የዋጋ ግሽበት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተና ሆኗል። ሪፎርም ባይደረግ ችግሩ መፍትሔ ሳያገኝ ይቀጥላል፡፡ ለምሳሌ ባለፉት 15 ዓመታት የዋጋ ግሽበት በአማካይ ከ15 በመቶ በላይ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ይህ ጤናማ ባለመሆኑ በሪፎርሙ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበትን ማስተካከል አንዱ ዓላማው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ 

ሌላው ባለፉት ዓመታት ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ቢመዘገብም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ከማረጋገጥ አንጻር ጉድለቶች ይታዩ ነበር፡፡ ሪፎርሙ ከሚፈጥረው ሀብት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጡ መሄድን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና ያሉ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ፈጣንና ተከታታይ እድገት ሲያስመዘግቡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን ከድህነት ማውጣት ችለዋል፡፡

ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደተሟላ ትግበራ የገባው ሁለተኛው ምዕራፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጥሩ ውጤት እያመጣ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አቶ ዘመዴነህ ያነሳሉ። የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓቱ በገበያ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን መደረጉ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተወሰደ አንዱና ዋነኛው እርምጃ ነው፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እንደሚያብራሩት፣ የምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን ከመደረጉ በፊት በህጋዊ ወይም ይፋዊ ገበያ አንድ የአሜሪካን ዶላር 58 ብር ሲመነዘር፤ በጥቁር ገበያው ደግሞ በእጥፍ ነበር የሚሸጠው፡፡ የመንግስት አካላት ካልሆኑ በስተቀር በህጋዊ መንገድ ዶላር ወደ ባንክ የሚያመጣ አልነበረም። ከውጭ የሚላከው ገንዘብ (ሪሚታንስ) ህጋዊ መስመር ተከትሎ አይመጣም ነበር፡፡ ወደ ውጭ ምርቶችን የሚልኩ ኩባንያዎችም የሚያገኙትን ዶላር ይደብቁ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሀገር እየተጎዳ፤ በጥቁር ገበያው የሚገበያዩ የተወሰኑ ሰዎች ሀብት እያከማቹ ነበር፡፡

የምንዛሪ ተመኑ በገበያ እንዲወሰን ከተደረገ በኋላ በመደበኛና ጥቁር ገበያው መካከል ያለው ምንዛሪ ተቀራርቧል፡፡ ሻጭና ገዥ እየተነጋገሩ የሚወሰን በመሆኑ በገበያው ግልፅነት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዲጨምር ይረዳል፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በሚዘጋጀው “ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ” የተሰኘው ዝግጅት ላይ ቀርበው “የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ጉዞና ተስፋዎች” በሚል ርዕስ ማብራሪያ የሰጡት የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥና የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባል ማሞ ምህረቱ ይህንን ሀሳብ ይደግፋሉ። “ይህንን ሪፎርም መተግበር ከጀመርን በኋላ ውጤቱን አሁን ብንመለከተው በኢኮኖሚው ውስጥ የሚደረገው የውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴ በአስገራሚ ሁኔታ አድጓል፡፡ በብሔራዊ ባንክና የፋይናንስ ተቋማት ያለው የምንዛሪ ክምችት በእጥፍ አድጓል” ሲሉ የተገኘውን ውጤት ያነሳሉ፡፡ በህጋዊ ገበያውና ጥቁር ገበያው መካከል ያለው የምንዛሪ መጠን ከሪፎርሙ በፊት እጥፍ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ከ7 በመቶ በታች ማድረስ ተችሏል፡፡

ከዚህ ባለፈ የግሉ ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ በበቂ ሁኔታ ማግኘት ችሏል። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ (ሪሚታንስ) በሚታይ መልኩ እድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

ሪፎርሙን ተከትሎ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ከታየባቸው ዘርፎች መካከልም የወጪ ንግድ ዘርፉ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለዚህም ባለፉት አምስት ወራት የተገኘውን አፈፃፀም ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ በ2017 በጀት ዓመት አምስት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል በ2016 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ102 በመቶ ጭማሪ አለው። ወርቅ፣ ቡና፣ ኤሌክትሪክ እና የቁም እንሰሳት ከዕቅዳችው በላይ አፈጻጸም ያስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች ናቸው፡፡ በአምስት ወራት ከቡና 797 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት እንደተቻለ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

ማሻሻያው የአምራች ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አቶ ዘመዴነህ ያነሳሉ፡፡

መንግስት የአምራች ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ነበር በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል ወደ ውጭ ምርቶችን የሚልኩ አምራቾች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ለራሳቸው የሚያስቀሩት የውጭ ምንዛሪ ወደ 50 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል። ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት 20 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ነበር እንዲወስዱ የሚፈቀድላቸው፡፡ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ያሉ ደግሞ ልከው የሚያገኙትን መቶ በመቶ እንዲወስዱ ተፈቅዷል፡፡

አቶ ዘመዴነህ እንደሚያስረዱት፣ ከዚህ ቀደም በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃና ማሽነሪዎችን ከውጭ ገዝቶ ለማስገባት የሚያስፈልጋቸውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ባንክ እየሄዱ ይሰለፉ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ውጭ ልከው ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ውስጥ ለራሳቸው የሚወስዱት ከፍ እንዲል በመደረጉ ቢዝነሳቸውን ለማሳደግ የሚያስፈልጋቸውን የግብዓት መግዣ ምንዛሪ በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። ለአምራቾች የታክስ እፎይታ በመስጠት፣ መሬት በማቅረብ፣ ብድር በማመቻቸት ድጋፍ እየተደረገ በመሆኑ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ትልቅ ዕድል ነው፡፡

የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር በኢኮኖሚው ትልቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ዘመዴነህ፣ የብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው የዋጋ ግሽበቱ ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረበት 35 በመቶ ወደ 16 ነጥብ 5 በመቶ ወርዷል፡፡

ይህንን በማስቀጠል ወደ አንድ አሃዝ ማውረድና መቆጣጠር ከተቻለ ትልቅ ለውጥ ነው። ሪፎሪሙ መልካም ውጤት እያመጣ የሚገኝ ሲሆን የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ፣ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፍቀድን ጨምሮ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ማሞ ምህረቱ እንዳብራሩት፣ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ የተያዙ ግልፅ ዓላማዎች እየተሳኩ መጥተዋል፡፡ ለዚህም ከወጪ ንግድና ከሬሚታንስ የሚገኘው ገቢ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እድገት እያሳየ መጥቷል የማዕድን፣ የአገልግሎት፣ የቱሪዝም፣ ሎጂስቲክስ፣ አቪየሽን ዘርፎችም ለውጥ እያሳዩ መጥተዋል፤ ወደፊት እያደጉ እንደሚመጡ ይጠበቃል የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰጠው ትኩረት ውጤት እያመጣ ነው፡፡ ይህም የዋጋ ንረትን መቀነስ ብቻም ሳይሆን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉም እድገት እንዲመጣ ያስችላል የሎጂስቲክስ፣ ባንክ፣ ቴሌኮም፣ ሀይል፣ ንግድና ችርቻሮ ዘርፎች ለግሉ ዘርፍ ክፍት መሆናቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ያስችላሉ፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review