AMN – ጥር 14/2017 ዓ.ም
የአእምሯዊ ንብረት ስራ የሀገር ኢኮኖሜ ግንባታ ላይ ጉልህ ድርሻ ያለው እና ኢንቨስትመንትንም የመሳብ አቅም ያለው በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣንን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የአእምሯዊ ንብረት ስራ የሀገር ኢኮኖሜ ግንባታ ላይ ጉልህ ድርሻ ያለው እና ኢንቨስትመንትንም የመሳብ አቅም ያለው በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ይህንን በመገንዘብ የተቋሙን አደረጃጀትና አሰራር ስርዓት በማዘመን የሪፎርም ስራዎችን በፍጥነት ተግባራዊ በማድረግ ፤ተቋሙ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይም በአለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እና በንግድ ምልክት፣በቅጅና ተዛማጅ መብቶች እንዲሁም በፓተንት መብቶች ዙርያ ኢትዮጵያውያን የፈጠራ ባለሞያዎችን የፈጠራ ውጤቶቻቸውን ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል እገዛ ከተቋሙ ይጠበቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመሰል በአለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶች ለአእምሯዊ ንብረት ስራ የሚኖረው ሚና ውሳኝ መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያም የተወሰኑ አለም አቀፍ ስምምነቶችን መፈረሟን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የፓሪስ ኢንዱስትሪያል ንብረት ጥበቃ ኮንቬንሽንን እና ዓለም አቀፍ የንግድ ምልክቶች ምዝገባ ፕሮቶኮልን በአዋጅ ማጽደቋን አንስተው የሪያድ ዲዛይን ህግ ስምምነት ሰነድን መፈረሟን አስታውሰዋል።
ባለስልጣኑ በሀገሪቱ ውስጥ ለአእምሯዊ ንብረት በቂ የህግ ጥበቃ እንዲኖር ለማስቻል ፣በፓተንት ሰነዶች ውስጥ የተካተቱ የቴክኖሎጂ መረጃዎችን ለመሰብሰብ፣ለማደራጀት እና ለማሰራጨት እንዲሁም አጠቃቀሙን ለማበረታታት ይሰራልም ብለዋል።
በተጨማሪም በአእምሯዊ ንብረት ላይ ፖሊሲዎችን እና ህጎችን ለማጥናት፣ ለመተንተን እና ለማማከር እንዲሁም በአእምሯዊ ንብረት ዙርያ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራን እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በተለያዩ የምርምር ተቋማት እና ተመራማሪዎች የሚከናወኑ የምርምር ውጤቶች በአእምሯዊ ንብረት መመዝገብ እንዳለባቸው ያለው አረዳድ አናሳ መሆኑ በአእምሯዊ ንብረት ምዝገባ ስራ ክፍተት እየፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በንግድ ምልክት፣በቅጅና ተዛማጅ መብቶች፣በፓተንት እና በጂኦግራፊያው ምንጭ አመልካች ምዝገባ ያከናወናቸው ስራዎች የተጎበኙ ሲሆን የፖተንት፣ የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ እና የቅጂ መብት እንዲሁም ተዛማጅ መብቶች አዋጆች በባለስልጣኑ የሚተዳደሩ መሆናቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።