
AMN- ጥር 15/2017 ዓ.ም
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ህገ-ወጥ ስደተኞችን ለመቆጣጠር በአሜሪካ እና በሜክሲኮ ድንበር 10 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮች ሊያሰፍሩ እንደሆነ ተገለፀ፡፡
አሁን ላይ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ድንበሩን በንቃት የሚጠብቁ 1 ሺህ 500 ወታደሮች ወደ አሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር በመላክ ላይ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ህገ ወጥ ስደተኞችን ከሀገር ከማስወጣት ባሻገር ስደተኞች ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያስችላቸውን የምዝገባ መርሐ-ግብርንም አቋርጠዋል።
የስደተኞች ማመልከቻዎችን የሚያስተናግደው ኤጀንሲ ያወጣው ማስታወሻ እንዳመላከተው፣ ወደ አሜሪካ የሚደረገው የስደተኞች ጉዞ ሙሉ በሙሉ ተሰርዟል።
የፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ እንደ ሀገር ቃል የገባንበትን ደህንነት፣ መጠለያ እና ከለላ የሚፈልጉ ሰዎችን ጉዳይ አጫልሟል ሲሉ የካሊፎርኒያ የስደተኞች ፖሊሲ ማዕከል ዳይሬክተር ማሲህ ፉላዲ ገልጸዋል፡፡
ከ150 ሺህ በላይ የሚሆኑ አፍጋኒስታናውያን በረራም እንዲሰረዝ መደረጉን ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በረራቸው የተሰረዘባቸው አፍጋኒስታናውያን ከ20 ዓመት በፊት ወደ አፍጋኒስታን በሄድንበት ወቅት እንደ አስፈላጊነቱ ከነበሩበት ሁኔታ እንደምናወጣቸው፣ ደህንነታቸውን እንደምጠብቅላቸው እና መኖሪያ ቤት እንደምናቀርብላቸው ቃል የገባንላቸው ነበሩ ሲሉም ፉላዲ ገልጸዋል፡፡