AMN-ጥር 22/2017 ዓ.ም
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ከሞሮኮው ናሽናል ራሊ ኦፍ ኢንዲፔንደንትስ(አር ኤን አይ) ፓርቲ ተወካይ ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ ጋር ተወያይተዋል።
የሞሮኮ ናሽናል ራሊ ኦፍ ኢንዲፔንደንትስ ፓርቲ ተወካይ ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለመታደም ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።
በዛሬው እለትም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል።
በውይይታቸውም የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጽናት ለቀጣይ ቁርጠኝነታችንን የምናድስበት ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር በመፈጸም የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምፅ መሆኑን በተግባር ማሳየቱንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲመዘገብ፣ የህዝቦች አንድነትና ትብብር እንዲጎለብት ብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ በፓርቲ ደረጃ ያላቸው ትብብርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የሞሮኮ ናሽናል ራሊ ኦፍ ኢንዲፔንደንትስ ፓርቲ ተወካይ ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ በበኩላቸው በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።
በመጀመሪያው ጉባኤ የተገባውን ቃል በመፈጸም ለዚህ የድል ምዕራፍ ስለደረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያና ሞሮኮ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን ገልጸው፣ በታዳሽ ሀይል፣ በግብርናና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጋራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
የደቡብ ለደቡብ ትብብር፣ የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን በማጠናከር በተፈጥሮ ሀብትና ሌሎች ዘርፎችም በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
በቀጣይም የብልጽግና ፓርቲ በሞሮኮ የሥራ ጉብኝት እንዲያደርግ ግብዣ በማቅረብ እንደ ፓርቲ ያላቸው ትብብርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።