በመዲናዋ በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በመዲናዋ በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – የካቲት 12/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ በ2017 ግማሽ ዓመት በኢኮኖሚያዊ እና በማህበራዊ ዘርፎች ውጤታማና እና ተስፋ ሰጪ ክንውኖች መመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በተለይም የመዲናዋን ሰላም ለማስጠበቅ ከህዝቡና ከጸጥታ መዋቅሮች ጋር የተሰራው ስራ፣ የገቢ አፈፃፀምን በማሻሻል ወጭን በመቆጠብ እና ብክነትን በመቀነስ እንዲሁም የኑሮ ውደነትን በማረጋጋት በኩል የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ የማጠናቀቅ አቅም ማደግ፣ የመሬት አስተዳደር፤ የንግድ አገልግሎት ስራዎች፤ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት፣ በጤና፣ በአሽከርካሪ ተሽከርካሪና የነዋሪዎች አገልግሎትን ለማዘመንና የሰው ተኮር ስራዎች አበረታች መሆናቸውንም ከንቲባ አዳነች አመላክተዋል፡፡

ከንቲባዋ አክለውም በስራ እድል ፈጠራ የመዲናዋን ነዋሪ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለመጨመርና ተኪ ምርቶችን ማምረት፣ የአረንጓዴና ውበት ስራዎች በበጀት አመቱ አጋማሽ በጥንካሬ የሚወሰዱ ናቸው ብለዋል።

ሆኖም ግን ከህብረተሰቡ አዳጊ ፍላጎትና እርካታ አኳያ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በተቋማት መካከል ያለውን የአፈጻጸም ስልቶችን ማቀራረብ፣ ብልሹ አሰራርና ጉቦኝነትን መቀነስ አሁንም ትግልና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ ቀሪ ወራትም ጥንካሬዎችን ይበልጥ በማጎልበት፡ ተግዳሮቶችን እየፈቱ፡ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች በቴክኖሎጂ፣ በአሰራርና በሰው ኃይል በማደረጀት አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አብራርተዋል፡፡

በተያያዘም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በከተማ ግብርና፣ በቤት ግንባታ፣ በውሃ አቅርቦት፣ በገቢ አሰባሰብ ማሻሻል፣ የሠላምና ፀጥታ ሥራ ማጠናከር፣ በትምህርት ለትውልድ፣ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም የለሙ ኮሪደሮችን አስተዳደር ማጠናከርና በ2ተኛው ዙር በ8 ኮሪደሮች የተጀመሩ ስራዎችን በጥራት፣ በጊዜ እና ወጭን በቆጠበ መልኩ አጠናቆ ለህዝብ አገልግሎት ለማዋል በልዩ ትኩረትና በርብርብ እንደሚሰራ ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review