AMN_የካቲት 18/2017 ዓ.ም
በዚህ ሳምንት መጨረሻ የኤፍ ኤ ዋንጫ የአምስተኛ ዙር ጨዋታዎች የሚደረጉ በመሆናቸው ፕሪምየር ሊጉ 27ኛ ሳምንት መርሃ ግብሩን ከዛሬ ጀምሮ ነው የሚያካሂደው፡፡
በዚህም ከምሽቱ 4 ሰዓት ተኩል በሚደረጉ ሶስት ጨዋታዎች የሚጀምር ይሆናል፡፡
በአሜሪካን ኤክስፕረስ ስታድየም ብራይተን በርንማውዝን የሚጋብዝበት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ፉልሃምን 2ለ0 ያሸነፈው ክሪስታል ፓላስ በሰልኸርስት ፓርክ አስቶን ቪላን ይጋብዛል፡፡
የቪላ ፓርኩ ክለብ ጠንካራውን ቼልሲን 2ለ1 ባሸነፈ ማግስት ነው ወደ ለንደን ተጉዞ የዛሬውን ጨዋታ የሚያደርገው፡፡
ዎልቭስ እና ፉልሃም በሞልኒክስ ስታድየም የሚያደርጉት ጨዋታ ከምሽቱ 4 ሰዓት ተኩል ላይ ይጀምራል፡፡
የዛሬ የመጨረሻው ጨዋታ በቼልሲ እና ሳውዛምፕተን መካከል የሚደረገው ሲሆን፣ ከምሽቱ 5 ሰዓት ከሩብ ሲል በስታንፎርድ ብሪጅ ይካሄዳል፡፡
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ በሁሉም ውድድሮች ከሶስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርገው ጨዋታ ነው፡፡
ቅዱሳኖቹ በበኩላቸው የውድድር ዓመቱን አስረኛ ወይም ደግሞ 12ኛ ነጥብ ለማግኘት የሚያደርጉት ጨዋታ ነው፡፡
ነገ መርሃ ግብሩ ሲቀጥል ማን ዩናይትድ ከኢፕስዊች፣ ኖቲንግሃም ከአርሰናል፣ ሊቨርፑል ከኒውካስትል ሲጫወቱ ሐሙስ የሚደረገው የዌስትሃም እና ሌስተር ጨዋታ የሳምንቱ መዝጊያ ይሆናል፡፡
በታምራት አበራ