እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ቬትናም፣ ማሌዢያ ያሉ ሀገራት የሰው ኃይል ሀብታቸውን አልምተው ከፍተኛ እድገት በማስመዝገብ የሕዝባቸውን ኑሮ ማሻሻል ችለዋል፡፡ ለዚህ ሁነኛ ተግባር ምክንያት የሚሆነው ደግሞ ትምህርትና ሥልጠና ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ በመዲናችን ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት አንዱ የሆነው የጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለኢንተርፕራይዞች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ በምን መልኩ እያደረገ እንደሆነና ያስገኛቸውን ውጤቶች እንመለከታለን፡፡
የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ ለማን ይሰጣል? የሚል ጥያቄ ያነሳንላቸው በኮሌጁ የቴክኖሎጂ ልማት እና የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ምክትል ዲን አቶ ደሜ መርሻ በምላሻቸው እንዳስረዱት ከሆነ፤ ድጋፉ በተለይም ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዦች እንደ ክፍተታቸው ሁኔታ እና መጠን በተለያዩ የስልጠና ማዕቀፎች በካይዘን (የጥራትና ምርታማነት ማሻሻያ)፣ በቴክኖሎጂ፣ በቴክኒካል የክህሎት ክፍተት ለይቶ ማብቃት እና በሂሳብ መዝገብ አያያዝና በሥራ ፈጠራ (ኢንተርፕርነርሽፕ) ዙሪያ ይሰጣል። በአሁን ሰዓትም ኮሌጁ ለ3 መቶ 44 ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
አቶ ደሜ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ መስጠት ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የዕድገት ደረጃና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ድጋፍ በመስጠት፣ ጥራትና ምርታማነታቸውን በማሻሻል ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። ኢንተርፕራይዞቹም በሚደረግላቸው ድጋፍ እና በሚያከናውኑት የምርታማነት እድገት መሰረት በላቀ የዕድገት ደረጃ ሽግግር እንዲያደርጉ ድጋፍ በማድረግ የማያቋርጥ የኢንዱስትሪ እድገት ማረጋገጥ በማስፈለጉ ነው፡፡
በተጨማሪም፤ ጥራቱንና ደህንነቱን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት እንዲሰጡ፣ የላቀ የዕድገት ደረጃ ሽግግር እንዲያደርጉ፣ በአምራች ኢንዱስትሪዎች የእድገት ደረጃ አወሳሰንና ሽግግር እንዲሁም በድጋፍ ማዕቀፍ አተገባበር ሂደት የሚታዩ ችግሮችን ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ሥርዓት በመዘርጋት እንዲፈቱ ማድረግ ለአስፈላጊነቱ ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡
የኢንተርፕራይዞች ጥራትና ምርታማነት እንዲሳለጥ ለማድረግ የካይዘን አሰራርን በውጤታማነት ተግባራዊ ማድረግ ለኢንዱስትሪው የሚኖረውን ፋይዳ በመገንዘብ በአሰራር እና ህግ ማእቀፍ መደገፍ ያስፈልጋል። የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነትና ውጤታማነትን ለማሳደግ፣ ያለውን ውስን ሃብት በፍትሐዊነት፣ በአሳታፊነት እና በተወዳዳሪነት መንፈስ ግልፅ አሰራር በመዘርጋት መተግበር በማስፈለጉ ኮሌጁ በቂ ስልጠናዎችን በባለሙያዎች አስደግፎ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
ከዛሬ አራት አመት በፊት የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ ተደርጎላቸው ስራቸውን በአግባቡ እና በተሻለ ሁኔታ መፈፀም ከቻሉት መካከል አቶ ታሪኩ ትሪ አንዱ ናቸው፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ፤ የቤት እና የቢሮ እቃዎችን በማምረት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ ከኮሌጁ ባገኙት ስልጠና ሥራቸውን በተሳለጠ አግባብ ለመከወን እንዳስቻላቸው የሚናገሩት አቶ ታሪኩ፤ በስራቸውም ውጤታማ መሆናቸውን ጭምር ተናግረዋል፡፡
ኢንተርፕራይዞችን በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ መስጠት እንደ ግለሰብ ያለውን አበርክቶ ከማጠናከር ባሻገር ለሀገራችንም ሁለንተናዊ እድገት ያለው አበርክቶ እጅግ የላቀ እንዲሆን ያደርገዋል። በስራቸው 20 ቋሚ ሰራተኞችን ቀጥረው እንደሚያሰሩ የሚናገሩት አቶ ታሪኩ፣ ለበርካቶች የስራ እድል ከመፍጠር በዘለለ ጥሩ የስራ ክህሎት ባለሙያዎች እንዲኖራቸው ከማድረግ አንፃር ኮሌጁ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
በኮሌጁ አማካኝነት ስልጠናዎችን በተለይ የሥራ እንዲሁም የህይወት ክህሎት ስልጠናዎችን ያገኙ ሰልጣኞች ተገቢውን ትምህርት ካገኙ በኋላ ወደ ግል ድርጅቶች ይላካሉ፡፡ ስራ እድልም እንዲመቻችላቸው የሚመለከተው የመንግስት አካል ከባለሀብቱ ጋር በማገናኘት ያስተሳስራል፡፡ በዚህም አቶ ታሪኩ በሙያው የሰለጠኑ ስራ ፈላጊዎችን በድርጅታቸው መቅጠር እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በኮሌጁ ሰልጣኞች የተሰሩ ማሽነሪዎችን በመግዛት ጭምር ለስራቸው ይጠቀማሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ከውጭ የሚገቡ ማሽነሪዎች ዋጋቸው ቀላል የሚባል ባለመሆኑ በሀገር ውስጥ በተለይም በኮሌጁ የተሰሩትን እቃዎች እንደ መፍጫ ማሽን፣ የማዳበሪያ ማሽን የመሳሰሉትን ገዝቶ ለተጠቃሚዎች ያንኑ ምርት በመሸጥ ሀብት እያፈሩበት መሆኑንም አክለዋል፡፡
የቢሮ እና የመስሪያ ቦታዎችን እንዴት በአግባቡ መጠቀም ይቻላል? የሚለውን ጭምር ጥሩ ትምህርት አግኝተውበታል። አሁን ላይ ካፒታላቸው 10 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ በቀጣይ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሸጋገር እቅድ እንዳላቸውም ጭምር አስረድተዋል፡፡
በኮሌጁ የቴክኖሎጂ ልማት እና የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ምክትል ዲን አቶ ደሜ በማብራሪያቸው፤ የኮሌጁ አሰልጣኞች እንደየሙያቸው በሥራ ላይ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ተገቢውን ስልጠና እየሰጡ ነው፡፡ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ፣ በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎት፣ በንግድ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ ለተሰማሩት ሙያዊ ስልጠናዎችንና ድጋፎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ አሰልጣኝ ከብረታ ብረት ጋር የተያያዘ ስልጠና የሚሰጥ ከሆነ፤ በዚህ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ተገቢው ሙያዊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ታች ድረስ በመውረድ ስራዎቻቸውን እንዴት እየከወኑ ይገኛሉ? የሚለውን በማየት ለውጥ እንዲያመጡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከድጋፍ አንፃር ኮሌጁ በቅርቡ በከተማ ግብርና በተለይም በከብት ማድለብ፣ በዶሮ እርባታ እንዲሁም በመኖ ማቀነባበር 15 ለሚሆኑ አንቀሳቃሾች ለአራት ቀን ሙያዊ ስልጠና ሰጥቷቸዋል። ለሁለት ቀን ደግሞ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ ተሰጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሰልጣኞችን የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሰዎች ልምድ እንዲለዋወጡ ማድረግ ተችሏል፡፡ በባለሙያዎች የሚደረገውን ድጋፍ በተመለከተ የክትትል አግባቡ በቴክኖሎጂ ልማትና ኤክስቴንሽን ስር ያሉ 16 ባለሙያዎች አሉ፡፡ በሳምንት አምስት ቀናት በቼክ ሊስት ስራዎችን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡
በኮሌጁ ያልተለመዱ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ እንዲሁም እንዲሰሩበት ከማድረግ አንጻር የተሄደበትን ርቀት አቶ ደሜ ሲያስረዱ፤ ቴክኖሎጂ ቁስ ብቻ ሳይሆን አሰራርም ጭምር ነው። በዚህም ኢንተርፕራይዞቹ ምርታቸው ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የአሰራራቸውና አደረጃጀታቸው ምን ሂደት መከተል እንዳለበት ድጋፍ እየተሰጠ ነው። ከዚያም ባለፈ በቁስ ደረጃ ያለቀለት ቴክኖሎጂ እንዴት መስራት እንደሚቻል የአቅም ግንባታ ስልጠናም እንዲሁ፡፡ ይህ ሲደረግ ስራው በብቃት ይሰራል፡፡
ለአብነት ያክል በፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ተሰርቷል። ምን አልባትም ማሽኑ ከውጭ የሚገባ ቢሆን በብር ሲገመት እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ሲሆን በውስጥ አቅም መሰራት በመቻሉ እስከ አራት መቶ ሺህ ብር ተሰርቶ ያልቃል፡፡ በዚህም ለሀገራችን የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት ረገድ ትልቅ ፋይዳን ያስገኛል፡፡ ኢንተርፕራይዞችም ማሽኑን ሞክረውት ጥሩ ሆኖ ስላገኙት የእርሱን አምሳያ ምርት እያመረትን እንገኛለንም ብለዋል፡፡
የኮሌጁን ቀጣይ የቤት ስራዎች በተመለከተም አቶ ደሜ ሲያብራሩ፣ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ እየሰጠ የሚገኘው ለሁለት ክፍለ ከተሞች ነው፤ ለጉለሌ እና አዲስ ከተማ፡፡ አሁንም የስራ ክህሎት ስልጠናውን በስፋት ለመስጠት አቅዷል፡፡ በክፍለ ከተሞቹ ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞችም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት ከመስጠት ባሻገር ሁሉንም ተደራሽ ያደረገ ስራ ለመስራት ውጥን ተይዟል፡፡ ኢንተርፕራይዞቹም በተሰማሩበት ስራ ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ የነገ ኢንዱስትሪ ተረካቢ እንዲሆኑ ተጠናክረን እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በሄለን ጥላሁን