ለናይሮቢ መነሳሳትን የፈጠረው የወንዝ ዳርቻ ልማት

You are currently viewing ለናይሮቢ መነሳሳትን የፈጠረው የወንዝ ዳርቻ ልማት

የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በናይሮቢ የወንዝ ዳርቻ ልማት አስጀምረዋል

በደረጀ ታደሰ

የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት መተግበር ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ውጤቱም ከወዲሁ እየታየ ይገኛል፡፡ በመዲናዋ እየተከናወነ ስለሚገኘው የወንዝ ዳር ልማት አስመልክቶ በቅርቡ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አስተያየት የሰጡት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ እንደጠቆሙት፤ በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ያለው የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት 51 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፤ ከእንጦጦ ተራራዎች ተነስቶ አቃቂ ወንዝ ድረስ የሚጓዝ ነው፡፡

የተጀመረው የወንዝ ዳርቻ ልማት ወንዞችን ከማልማት ጋር ተያይዞ ለዓመታት ሲቀርብ የቆየውን የከተማዋን ነዋሪዎች ጥያቄ የሚመልስ ነው ያሉት አቶ ጥላሁን፤ አዲስ አበባን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ፣ የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ፣ የህዝብ መናፈሻ ፓርኮችን ለማበራከት፣ የብስክሌትና የመሮጫ መንገዶችን ለመፍጠር፣ የከተማዋን ዕይታ በመለወጥ የህብረተሰቡን ደህንነት ለማሻሻል፣ በልማቱ ላይም ሆነ ከልማቱ በኋላ በርካታ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ አቅምን የፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

ከእንጦጦ ተራራ በጉለሌ በኩል እስከ አፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ እንዲሁም ከእንጦጦ በአፍንጮ በር አልፎ በባንቢስ አድርጎ እስከ አቃቂ የውሃ ማጣሪያ በሚደርሰው የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት 28 ድልድዮች ይሰራሉ፤ ከዚህ በተጨማሪም ሰው ሰራሽ ሐይቆች፣ አረንጓዴ ቦታዎች፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የውኃ ትራንስፖርት እና የንግድ ማዕከላት ይገነቡበታል፡፡ የእግር ጉዞ ማድረጊያና የመሮጫ ትራኮች፣ የብስክሌት መስመሮች፣ ኬብል ካር ትራንስፖርት (የገመድ ላይ መኪና)፣ መዝናኛ ግድቦችን እውን ለማድረግ ያለማቋረጥ 24 ሰዓት በሚተጉ ዜጎች እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪድር ልማት እና የወንዝ ዳር ልማት ሥራዎችን እንቅስቃሴ ከሁሉም የኮሪደር ልማት አስተባባሪዎች ጋር በመሆን ለሁለት ቀናት የጎበኙት እና በአፈፃፀማቸው ላይ ግምገማ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ “ከተማውን በመበከል የህዝቡን ጤና በመጉዳት ከፍተኛ አሉታዊ ጉዳት ሲያደርሱ የነበሩትን ህግ እና ስርዓት አውጥተን  የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት በከፍተኛ ደረጃ እየተገበርን ነዉ። የወንዞችን ብክለት በመከላከል በኩል ጽዱ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ለመፍጠር  የብክለት መከላከል ህግ ህብረተሰባችን መቀበሉን እና እየተገበረው መሆኑን በጉብኝታችን ወቅት ተመልክተናል” ብለዋል፡፡

አክለውም፤ በተሰጣቸው ጊዜ ገደብ ውስጥ ያልገነቡ እና የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓታቸውን ያላስተካከሉትን ከተማ አስተዳደሩ በመቅጣት ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ከቅጣቱ በላይ ነዋሪው ለራሱ ጤና ሲል የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓቱን እና ብክለት መከላከልን እንዲተገብር አሳስበው ለሥራው ውጤታማነት ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አጠቃላይ ሁኔታን በተመለከተም ባሰፈሩት መረጃ ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን የዘረዘሩ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 42 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የወንዝ ዳርቻ እና 431 ሄክታር የሚሸፍን የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ይገኙበታል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ቀን ከሌሊት የተተገበሩ እና እየተተገበሩ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በውጤታቸው ከአገር አልፎ ሌሎችንም ማንቃታቸውን ቀጥለዋል፡፡ አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ የተመቸች፣ ፅዱ እና ምቹ፣ ዘመናዊነትን የተላበሰች ጎብኚዎችን የምትስብ እና ቆይታቸውን የምታራዝም ለመሆን ያላትን ርዕይ ከወዲሁ እያሳካች ትገኛለች፡፡ የተጀመሩት የ2ኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራው ሲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ደረጃ አሁን ካለበት በእጅጉ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት እያስገኘ ያለው ተጨባጭ ውጤት ነፀብራቁ ወደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከተሞች መዳረስ የጀመረ ይመስላል፡፡ የኬኒያ እና የደቡብ አፍሪካ የሰሞኑ እንቅስቃሴ ይህንኑ እውነት የሚያረጋግጥ ሆኗል፡፡ የጎረቤት ሀገር ኬኒያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ይፋ ያደረጉት የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት አንድ ማሳያ ነው፡፡

ባሳለፍነው ሰኞ ዕለት ይፋ የሆነውና ናይሮቢ ይከናወናል ተብሎ የታቀደው የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት የከተማዋን ውበት፣ ፅዳት እና ለኑሮ ያላትን የምቹነት ደረጃ ከፍ እንደሚያደርግ፣ የትራንስፖርት መሰረተ ልማትን እንደሚያዘምን እና የነዋሪውን እንቅስቃሴ እንደሚያቀላጥፍ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኚዎች የምትመች የነቃች ከተማ እንድትሆን ለሚያግዘው ፕሮጀክት 50 ቢሊዮን የኬኒያ ሽልንግ በጀት ተይዞለታል፡፡

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ፕሮጀክቱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ “በሚቀጥሉት 24 ወራት ውስጥ በናይሮቢ እጅግ ፅዱና የሚያማምሩ ወንዞችን እንመለከታለን። የወንዞች መልሶ የማልማት ሥራው 50 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት፣ የትራንስፖርት እና መሰል አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶችን ባካተተ መልኩ የሚተገበር ነው፡፡ 60 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ዝርጋታም የፕሮጀክቱ አንድ አካል ተደርጎ ይተገበራል፡፡ ፕሮጀክቱ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል፣ ጤናማ፣ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ከባቢን ዕውን ለማድረግ ያግዛል” ብለዋል፡፡

ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ኬኒያዊያን የበኩላቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ፕሬዝዳንት ሩቶ ብሔራዊ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ይፋ በሆነበት ወቅት በስፍራው ከተገኙት የቀድሞው የኬኒያ  ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና ከሌሎች መሪዎች ጋር ለሀገሪቱ አንድነት እና ብልጽግና በጋራ ለመስራት መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካውያን መዲና የሆነችው አዲስ አበባ የአህጉሪቱን መሪዎች አዲስ ዕይታ የመግለጥ አቅሟን ለኬኒያ ብቻ ሳይሆን ለደቡብ አፍሪካም አሳይታለች። በቅርቡ ለአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት ከተማዋን ተዘዋውረው የመጎብኘት ዕድል ያገኙት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪሊ ራማፎሳ በአዲስ አበባ አስደናቂ ለውጥ ተደምመዋል፡፡ መደመማቸውን በአገራቸው ከተሞች ላይ ለመተግበርም አነሳስቷቸዋል፡፡ ለዚህም ነው፤ ከአዲስ አበባ እንደተመለሱ፤ “ጆሀንስበርግ እንደ አዲስ አበባ እንድትሆን እንሠራለን” የሚል መልዕክት ለሕዝባቸው ያስተላለፉት፡፡

ጆሃንስበርግ እንደ አዲስ አበባ ሆና የማየት ፍላጎታቸውን ይፋ ያደረጉት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት፤ ይህንን ያሉት በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የጆሀንስበርግ ከተማ የምታስተናግደውን የጂ 20 የመሪዎች ስብሰባ ቅድመ ዝግጅትን አስመልክቶ መልዕክት ባስተላለፉት አጋጣሚ ነው፡፡ በንግግራቸው፤ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች በቀን እና በምሽት በምቹ ጎዳናዎች ላይ እንደልባቸው መንቀሳቀስ እንደሚችሉም መስክረዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review