AMN-መጋቢት 12/2017 ዓ.ም
በኢንዶኒዢያ በተካሰተው የእሳት ጎመራ ፍንዳታ ምክንያት አመዱ 8 ኪሎ ሜትር ከፍታ ጉም በመፍጠሩ በአካባቢው አንዳንድ በረራዎች መሰረዛቸው ተገልጿል፡፡
በኢንዶኒዢያ ደቡብ ምስራቃዊ ክፍል በፍሎሬስ ደሴት በሌዎቶቢ ላኪ ተራራ የተከሰተው የእሳተ ጎመራ ፍንዳታ ያመነጨው አመድ 8 ኪሎ ሜትር ከፍታ ድረስ ጉም በመፍጠሩ ለበርካታ በረራዎች መሰረዝ ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር፣ ለአካባቢው ነዋሪዎች እና ለጎብኚዎች የአስቸኳይ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡
የሀገሪቱ የስነ-ምድር እና እሳተ ጎመራ አደጋ መከላከል ማዕከል፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ጎብኚዎች እሳተ ጎመራው ከተከሰተበት ሥፍራ ደቡብ ምዕራብ እና ሰሜን ምሥራቅ ክልለ ከ7 እስከ 8 ኪሎ ሜትሮች እንዲርቁ አስጠንቅቋል፡፡
ማዕከሉ ትናንት ማታ የተቀሰቀሰውን እሳተ ጎመራ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ አመዱ ጥቅጥቅ ያለ ጥቁር-ግራጫ መልክ ያለው ደመና መፍጠሩን አመላክቷል፡፡
እስከ አሁን አደጋው በአቅራቢያ ባሉ መንደሮች ላይ ያደረሰው ጉዳት ባይገለጽም፣ ማዕከሉ ግን በአካባቢው እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ የተነሳ በቅልጥ አለቱ ጉዳት እንዳያደርስ ተጋላጭ ነዋሪዎችን ማስጠንቀቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በታምራት ቢሻው