የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ከትናንት በስቲያ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል። የምክር ቤት አባላት የፌዴራል መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የአፈፃፀም ሪፖርትን መነሻ በማድረግ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምንና ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት እየተሰሩ ባሉ ስራዎች፣ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አተገባበር፣ የባህር በር፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተነሱት ፖለቲካዊ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ በተለያዩ አንጓዎች በመከፋፈል ለንባብ በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ሰላምና ፀጥታን በተመለከተ
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችና የሰላም እጦትን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ ግጭትን ላዩን ሳይሆን መዋቅራዊ ችግሩን በመገንዘብ ነው መፍታት የሚቻለው፡፡ በምርጫና በህዝብ ይሁንታ የተመረጠ፣ በብቸኝነት ሀይል የመጠቀም ስልጣን ያለውን መንግስት “በሀይል እንጥልሃለን” ሲሉት በዝምታ ማለፍ የለበትም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሁለት መሰረታዊ የፖለቲካ ስብራቶች አሉ፡፡ አንደኛው የመጠፋፋት ባህል ነው፡፡ መንግስታት ወደ ስልጣን ሲመጡ “አልጋው ሳይፀና” እናፍርሰው የሚሉ ኃይሎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስታት በሰላማዊ መንገድ ሽግግር ያደረጉበት ታሪክ የለም፡፡ ሁለተኛው ከሶሻሊዝም እሳቤ ጋር ተያይዞ የመጣው የፍረጃ በሽታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የፓርቲ ፖለቲካ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመደራደር የመፍታት ልምምዱ የለም ነው ያሉት፡፡
“በሀይል ስልጣን መያዝን አቅልሎ የመመልከት ችግር አለ፡፡” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ነውጠኛ ነፃ አውጪ ነን የሚሉ ታጣቂዎች፣ በመጀመሪያ ደረጃ ሰለባ የሚያደርጉት “እንታገልልሃለን” የሚሉትን የራሳቸውን ህዝብ ነው፤ ለሚታገሉለት ህዝብም ዕዳ ናቸው ብለዋል፡፡
ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትን ማክበር ጋር በተያያዘም ከተፎካካሪ የምክር ቤት አባሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ለተነሳው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ መንግስት ለትችት ክፍት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ ስልክና ማይክራፎን ስላለው ሁሉም እንዳሻው የሚናገርበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡ በዚህ ረገድ በእስር፣ ክስና ሌሎች ጉዳዮች መታረም ያለባቸው ጉዳዮች ካሉም እንፈትሻለን ሲሉ መልሰዋል፡፡
ወደኋላ መለስ ብለን የኢትዮጵያን የአንድ መቶ ዓመት ታሪክ ብናይ ባለፉት ሰባት ዓመታት አንድም ጊዜ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጦርነት ያልገጠመ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ነ። ነገር ግን የሚያጋጩ ጉዳዮች ስለሌሉ ሳይሆን ግጭት ጉዳት ስለሚያመጣና ስለማንወድ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በሶማሊያ ክልሎች ካሉ ታጣቂዎች ጋር በመደራደር ወደ ሰላም እንዲመጡ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
የእስረኞች አያያዝን በተመለከተም፣ የፓርላማ አባላት ሳይቀር በየጊዜው እንደሚጎበኟቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ድሮ እንኳን ፓርላማ ሊጎበኛቸው ታሳሪዎች ከእስር ሲፈቱ እንኳን የት ቦታ ታስረው እንደቆዩ አያውቁም ነበር፤ ተሸፍነው ገብተው ተሸፍነው ይወጣሉ፡፡ አሁን ተሻሽሏል። ነገር ግን አሁንም የሚቀሩ ነገሮች እየታረሙ ይሄዳሉ ሲሉ አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር አካታች ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ በተለያየ ጊዜ ግፊት ሲደረግበት የቆየ አጀንዳ ነው። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አጀንዳቸውን በነፃነት እያቀረቡ ይገኛሉ፤ ጠቃሚ ስለሆነ ውጤታማ እንዲሆን መንግስት ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ጋር ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ድርድር ተደርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም ከኦነግ ሸኔ አንድ ክንፍ ጋር ድርድር ተደርጎ በሰላማዊ መንገድ ገብተዋል፡፡ የተቀሩት ጋርም መንግስት በሰላምና ድርድር ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላምና እድገት ለሚጓጉ ግለሰቦችና ቡድኖች መንግስት ለንግግር በሩ ክፍት መሆኑን ተገንዝበው ጉዳያቸውን በዚህ አግባብ ለመፍታት መዘጋጀት አለባቸው ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የፕሪቶሪያ ስምምነት አተገባበርን በተመለከተ
በፌዴራል መንግስትና ህወሓት መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ታሪካዊና ለብዙዎች ልምድ የሚሰጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ እየተዋጋና እያሸነፈ ለሰላምና ድርድር የሚቀመጥ መንግስት የለም፡፡ ይህ እንዲሆን ያደረገው መንግስት ሰላም ስለሚፈልግ ነው፡፡ ድርድሩም ለትግራይ ህዝብ ከፍተኛ ጥቅም አምጥቷል ብለዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት የሚጠበቁ ግን በበቂ ሁኔታ ያልተፈፀሙ ጉዳዮች እንዳሉ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማቋቋም በተሟላ መንገድ አልተፈፀመም፡፡ ይህ አለመደረጉ በመጀመሪያ የሚጎዳው የትግራይን ህዝብ እንደሆነ ጠቅሰው እንዲፈፀም መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የተፈናቀሉትን በመመለስ ረገድ በራያና ጸለምት አካባቢ ጥሩ ስራ ተሰርቷል። በወልቃይት የተጀመሩ ጉዳዮች በተፈለገው ደረጃ አልሄዱም። የፌዴራል መንግስት ተፈናቃዮችን ለመመለስ ዝግጁ ነው። የተፈናቀሉ ሰዎችን ጉዳይ ከፖለቲካ በመነጠል ሰብዓዊነትን ባስቀደመ መልኩ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጦርነት እንዳይነሳና ጥያቄዎች በንግግር እንዲፈቱ በማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። አሁን የተሰጣቸው ጊዜ ስላለቀ የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት ባከበረ መንገድ የህግ ማሻሻያ በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እስከሚቀጥለው ምርጫ ስራውን እየሰራ እንዲቀጥል በማድረግ ህዝቡን ለምርጫ ማዘጋጀት ይጠበቃል፡፡
ለዚህም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ከህወሓትና ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ንግግሮች እየተካሄዱ ነው፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አፈጻጸም ተገምግሞ በግለሰቦች ደረጃ ለውጥ ይኖራል፡፡ የትግራይ ህዝብ ከዚህ በኋላ ጦርነት አይፈልግም፡፡ በትግራይ ያለው ችግር በንግግርና ውይይት ይፈታል፡፡ ከሁሉም ሀይሎች ጋር ንግግር እየተደረገ በመሆኑ ሲጠናቀቅ ለህዝብ ይፋ ይሆናል ሲሉ በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ አብራርተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ ግድቡ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ነው፡፡ አንድ ብር ብድርም ሆነ እርዳታ ያልወሰድንበት፤ ብዙ ፈተና ያየንበት ነው፡፡ በነበረው የፀጥታ ችግር ከሁለት ወር ተኩል ያላነሰ ጊዜ ለግድቡ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን ከጂቡቲ እስከ ግድቡ የሚገነባበት ቦታ እያጀብን እየወሰደን ነው የሰራነው። ግድቡን ቢበዛ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ጨርሰን ሪቫን እንቆርጣለን። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ታሪክ ይሆናል ብለዋል፡፡
በግድቡ ዙሪያ ከግብፅ የሚነሳው ስጋት ጋር በተያያዘም፣ የውሃ ፍሰት በድርቅ ወቅት እንዳይቀንስ ከኢትዮጵያ ጋር ችግኝ በመትከል በትብብር መስራት ያስፈልጋል፡፡ ከግብፅ ጋር በውይይትና በትብብር አብረን ብንሰራ ሁለቱም ህዝቦች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ለውይይትና ትብብር በሩ ክፍት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ይዟል፡፡ ህዳሴ የአፍሪካ ኩራት ነው። ለመላው አፍሪካ መቻልን ያሳየንበት፣ በውስጣችን ያለውን ስህተት ጨክነን ወስነን ያረምንበት ነው፡፡ አፍሪካውያን ብድር ቢከለከሉ፣ የዲፕሎማሲ ጫና ቢደረግባቸው የራሳቸውን ሀብት በራሳቸው አቅም ማልማት እንደሚችሉ በተግባር የሚያስተምር ስራ ነው ሲሉም ግድቡ ላይ የታየውን የመተባበር መንፈስ አብራርተዋል፡፡
የባሕር በር
የባህር በርን ጥያቄ ማንሳት ነውርነቱ አክትሟል፡፡ ከማንም ሀገር ጋር ስንነጋገር ጥያቄው ትክክል እንደሆነ ነው የሚናገሩት። “የእናንተን ያህል የህዝብ ቁጥር ኖሮት የባሕር በር የሌለው የለም” ነው የሚሉት። ይኽም ለኢትዮጵያ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል፡፡
ሰሞኑን በባሕር በር ጉዳይ ኢትዮጵያ ከኤርትራ መንግስት ጋር ወደ ግጭት ትገባለች የሚሉ ስሞታዎች ይነሳሉ። ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የላትም፡፡ ፍላጎቷ በሰጥቶ መቀበል፣ ህዝቦችን በሚጠቅምና በገበያ መርህ እንነጋገር ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ክሶች ውሃ የሚቋጥሩ አይደሉም ነው ያሉት፡፡
የቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ 130 ሚሊዮን ህዝብ፣ ኢኮኖሚው እያደገ ያለ፣ መለወጥና ከድህነት መውጣት የሚፈልግ ሀገር ተዘግቶበት እስር ቤት ሊቀመጥ አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ከወንድምና እህት ጎረቤት ህዝቦች በህግና በሰጥቶ መቀበል መርህ የኢትዮጵያ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ያድርግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢኮኖሚን በተመለከተ
ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱላቸው ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል፡የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት፣ የግብር ገቢ አሰባሰብ ስርዓት፣ የፕሮጀክት አፈፃፀም እና ተያያዥ ጉዮች ይጠቀሳሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጥያቄዎቹን መነሻ በማድረግ እንደ ሀገር በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ፣ ውጤቱንና ተግዳሮቶቹን በአሀዛዊ መረጃ በማስደገፍ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት በዋና ዋና የኢኮኖሚ አመላካቾች ታላላቅ ስኬቶች ተመዝግበዋል። በቀሪ ወራት ይህን ስኬት ማጠናከር ከተቻለ ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት ከ8 ነጥብ 4 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት እንደምታስመዘግብ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አብዛኛው የእርሻ ማሳ በአነስተኛ እና በመካከለኛ ደረጃ ላይ በሚገኙ አርሶ አደሮች በተያዙ የእርሻ መሬቶች ላይ እየተከናወነ የሚገኘው የግብርናው ዘርፍ አበረታች ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህንን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንደጠቆሙት፤ በግብርና ምርት የአነስተኛ አርሶ አደሮች የሰብል ሽፋን 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል። በስንዴ ልማትም በመኸር 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር እንዲሁም በበጋ መስኖ ልማት 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ የተሸፈነ ሲሆን፤ በዚህም ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል። በቡና እና ሻይ ምርትም የተሻለ ስኬት እየተመዘገበ ነው። ለአብነትም ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ከቡና ወጪ ንግድ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
ሌላኛው በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ የሚገኘውን የኢንዱስትሪው ዘርፍ አስመልክቶ የሚከተለውን ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ ያሉ ማነቆዎችን የመፍታት ስራ ሲከናወን ቆይቷል። በዚህም የውጭ ምንዛሬ፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች ችግሮች የተለዩ ሲሆን ችግሮቹን ለመቅረፍም እየተሰራ ነው። ለአብነትም በዘንድሮው ዓመት ብቻ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ የቀረበው የኃይል አቅርቦት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ50 በመቶ ብልጫ አለው። ከጥቂት ዓመት በፊት የአቅርቦት ጥያቄ የነበረበት የሲሚንቶ ምርትም አሁን ላይ ለውጭ ገበያ ጭምር ማቅረብ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው። የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 61 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ብቻ 55 አዳዲስ ፋብሪካዎች ስራ ጀምረዋል።
“ባለፉት ስምንት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ580 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስት የሚሰበስበው ገቢ ከጥቅል ሀገራዊ ምርት አንጻር ከ7 በመቶ እንደማይበልጥ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከገቢ የምትሰበስበው ገንዘብ መጠን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይህን ክፍተት ማሻሻል እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ በየአከባቢው የሚቀርቡ የልማት ጥያቄዎችን መመለስ የምንችለው ገቢያችንን በበቂ ሁኔታ ማሳደግ ሲቻል ብቻ ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡
የዋጋ ንረትን አስመልክቶ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ ድጎማ በማድረግ የዋጋ ንረቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች እንዳይጎዳ በጥንቃቄ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል። ይህን በምሳሌ ሲያስረዱ፤ መንግስት በአንድ ኩንታል ማዳበሪያ 3 ሺህ 700 ብር፣ ለነዳጅ በሊትር 28 ብር ይደጉማል። ለነዳጅ ብቻ በድምሩ 72 ቢሊዮን ብር ድጎማ መደረጉን አንስተዋል፡፡ የደመወዝ ጭማሪ በማድረግም ቋሚ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ገቢያቸው እንዲያድግ እየተሠራ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚሠራው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወደማጠናቀቂያው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ እና በመጪው መስከረም ወር አካባቢ ሪቫን እንደሚቆረጥ ያበሰሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ እንደ ህዳሴ ግድብ ሁሉ የኢትዮጵያ ቀጣዩ ታላቅ ስራ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት እንደሚሆን ይፋ አድርገዋል፡፡ “ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመር አለብን” ብለን ስራ ጀምረናል። ይህን ስራም በተለይ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተሳሰር ለመስራት መታሰቡን ገልፀዋል፡፡ አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያ በየዓመቱ 24 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ የሚያስፈልጋት ሲሆን፤ ይህን ፍላጎት ለሟሟላትም በየቀኑ 150 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እያጓጓዝን ነው ብለዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ ባለፉት ስምንት ወራት ከ3 ሚሊዮን በላይ ሠዎች ስራ ተፈጥሯል፡፡ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ዘርፎች ናቸው፡፡ የሥራ ባህልም እየተሻሻለ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በውጤታመነቱ የተተገበረውንና እየተተገበረ ያለውን የኮሪደር ልማትን በተመለከተም፤ “ከዛሬ ባሻገር ቀጣዩ ትውልድን መሰረት ያደረገ ነው። በአዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ተሰርቷል። ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶችም ተከናውነዋል። ባለፉት አምስት አመታት ከ30 ሺህ በላይ የተሸከርካሪ ማቆሚያ (ፓርኪንግ)፣ 167 ሺህ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ ዜጎች ያላቸውን ሃብት ዋጋ (አሴት) ከፍ አድርጓል። በኮሪደር ልማቱ ለተነሱ ዜጎችም በቂ ካሳ ተከፍሏል። እስካሁን ባለው ሂደትም ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ ተከፍሏል። በሁሉም የክልል ከተሞችም አስደማሚ ስራ እየተከናወነ ነው፤ ለአብነትም በሐረር ከተማ በዜጎች ተሳትፎ የተከናወነው ስራ ምሳሌ የሚሆን ነው” በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩና ደረጀ ታደሰ