ሀገራዊ ለውጡ በኢትዮጵያ የባለቤትነት ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም መያዝ አስችሏል – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )

You are currently viewing ሀገራዊ ለውጡ በኢትዮጵያ የባለቤትነት ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም መያዝ አስችሏል – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )

AMN – መጋቢት 25/2017

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የለውጡን ሰባተኛ አመት አስመልክቶ በተገኙ ትሩፋቶች እና ባጋጠሙ ፈተናዎች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የለውጡ መንግስት ከመመስረቱ በፊት በነበሩት ዓመታት የተስተዋሉ የፍትሀዊነት፣ የአሳታፊነት፣ የእኩልነት እና መሰል ችግሮች በሀገሪቱ የፖለቲካ ሪፎርም እንዲፈጠር ምክንያት ስለመሆኑ አንስተዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በመደመር መንገድ ተጉዞ ለውጡ የሚመራበትን አስተሳሰብ፣ግልጽ ራዕይ እና መላውን ህዝብ ያሳተፈ ስለመሆኑ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ ወደ ተግባር ስለመገባቱም አብራርተዋል።

በለውጡ ከተገኙ ትሩፋቶች ውስጥ አንዱ የፖለቲካ ሪፎርም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በኢትዮጵያ የባለቤትነት ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በኢኮኖሚ ላይ የተደረገ ማሻሻያ ሌላኛው ትሩፋት መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ወታደራዊ አቅም እና የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ማጎልበት ወሳኝ ናቸው ብለዋል።

በሀገሪቱ ያሉትን ጸጋዎች በመጠቀም በሙሉ አቅም በማምረት ከውጭ እርዳታ ይልቅ በራስ አቅም የማደግ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

ከተሞች ለህዝብ መኖሪያነት ምቹ እንዲሆኑ የኮሪደር ልማት ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ ባለፈ የገቢ አቅምን በማሳደግ ረገድ የላቀ ሚና እንዳለውም ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው አመላክተዋል።

የቱሪዝም እና የማዕድን ሀብት ጸጋዎችን ማጠናከር በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑም አመላክተዋል።

የኑሮ ውድነትን ለመከላከል የማምረት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በሁሉም መስክ የስራ እድል ፈጠራን ማጠናከር እንደሚገባም አብራርተዋል።

ያገኘናቸውን ድሎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከነጠላ ወደ ገዢ ትርክት መሸጋገር ተገቢ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው ማብራራታቸውን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review