የመደመር መፅሐፍ  ሰበዞች

You are currently viewing የመደመር መፅሐፍ  ሰበዞች

‘የመደመር መንገድ’ በሚል ርዕስ በ2013 ዓ.ም ለንባብ የበቃው የጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጽሐፍ  በይዘቱም ሆነ በአቀራረቡ ለየት ይላል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የልጅነት ትውስታቸውን ይተርካሉ፡፡ በተለይ ስለ አስተዳደጋቸው፣ ከእናትና አባታቸው ጋር የነበራቸው የልጅነት ጊዜ፣ በኋላም ወደ ትግል የገቡበት አጋጣሚ፣ በኢህአዴግ ቤት ያሳለፉትን ጥሩና ጥሩ ያልሆኑ ጊዜያትን ያወሳሉ፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ስላደረጓቸው ትግሎች በዚህ መጽሐፋቸው በስፋት ያብራራሉ፡፡ የመደመር ዕሳቤ መሰረትና የብልጽግና ፓርቲ ከጥንስሱ አንስቶ እስከ ምስረታው ድረስ በወፍ በረር በመጽሐፉ ውስጥ ትኩረት ያገኙ ጉዳዮች ናቸው። በዚህ አምድም ‘የመደመር መንገድ’ በተሰኘው የዐቢይ (ዶ/ር) መጽሐፍ ውስጥ ከተካተቱ ሰዋዊና ሀገራዊ አንኳር ጭብጦች ላይ አጭር ዳሰሳ አድርገናል፡፡    

‘የመደመር መንገድ’ ሦስት ክፍሎች አሉት፡፡ እያንዳንዱ ክፍል በተለያዩ ምዕራፎች  ተከፋፍሏል፡፡ በዚህ መሰረት መጽሐፉ አስራ አንድ ምዕራፎች ይዟል። ክፍል አንድ፣ አምስት ምዕራፎችን የያዘ ሲሆን፣ የመጽሐፉ ዋነኛ ሊባሉ የሚችሉት ሃሳቦች ቀርበውበታል፡፡ ክፍል ሁለትና ሦስት ደግሞ እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ምዕራፎችን ይዘዋል፡፡

‘የመደመር መንገድ’ መጽሐፍ ከሥነ-ጽሑፋዊ፣ ከፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም እና ከፍልስፍና አንጻር ሊታዩ የሚችሉ ርዕሰ-ጉዳዮችን ዳስሷል፡፡ ይህ መጽሐፍ 439 ገጾች ያሉት ሲሆን፣ ከአማርኛ በተጨማሪ በኦሮምኛ ቋንቋ ታትሞ ነው ለንባብ የበቃው፡

የሮቦት ፖለቲከኝነት

‘የመደመር መንገድ’ መጽሐፉ በደረቅ የፖለቲካ ቃላትና ጽንሰ-ሃሳቦች የታጨቀ መጽሐፍ አይደለም። ሰዋዊነት ጎልቶ ይታይበታል፡፡ ማለትም፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅነት፣ አስተዳደግና የተወለዱበት ስፍራ በሻሻ ምስል በሚከስት አኳኋን በመጽሐፉ ተዳስሷል። ከዚህ ቀደም በመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ግለ ታሪክና የሕይወት ታሪክ ላይ ስለ ግለሰቡ ህይወትና አስተዳደግ ትኩረት ሰጥቶ ሲተረክ ብዙም አይታይም፡፡ 

በሀገራችን ፖለቲከኞች አልፎ አልፎ የሚጻፉ መጽሐፎችን ላስተዋለ፣ ሰውዓዊ ፍላጎቶችን ወደ ኋላ በመግፋት የፖለቲካ ተሳትፎና ተያያዥ ጉዳዮችን የማጉላት ዝንባሌ መታዘቡ አይቀርም፡፡ ይህ አይነት አቀራረብ የሚከተሉ ፖለቲከኞች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጽ “የሮቦት ፖለቲከኞች” መገለጫዎች ናቸው፡፡ ስሜት አልባ መስሎ መታየት ሰውዓዊ ለሆኑ ጉዳዮች ትኩረት መንፈግ ነው “የሮቦት ፖለቲከኝነት” መገለጫ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠሩት፡፡ በአንጻሩ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ዐቢይ (ዶ/ር) በአብዛኛው ሰውዓዊ አቀራረብ ነው የተከተሉት፡፡ ለአብነትም ሰው ሰው የሚሸቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትውስታዎች፣ ወጎችና ቀልዶች ተካትተውበታል፡፡ ከትውስታ አንጻር “ትንሹ ዐቢይ በበሻሻ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር የዐቢይ (ዶ/ር)  የልጅነት ጊዜ ተተርኮበታል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ልጆች በአብዛኛቸው ለእናታቸው ይቀርባሉ፡፡ ከውልደት አንስቶ እስከ ጉርምስና ዕድሜ ድረስ ልጅ ከእናቱ ጥላ ስር ብዙም አይርቅም። ቁጣውም ፍቅሩም፤ ሚስጥሩም የአደባባይ ዕውነታውም እናቶች በበለጠ ይገነዘቡታል፡፡ በአንጻሩ አባት ከእናት ይበልጥ ይፈራል፡፡ ከእናቶች ተግሳጽ ይልቅ የአባቶች ኮስታራነት ያስፈራናል። በተለያዩ ባህሎች ውስጥ ብናድግም፣ የልጅነት ጊዜያችን ከፍ ያለ ምስስሎሽ ይንጸባረቅበታል፡፡ የዚህ ምክንያት በልጅ አስተዳደግ ውስጥ የእናቶች ሚና በጣም ተመሳሳይነት ስላለው ይመስላል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደግም ይህንን ፈለግ የተከተለ ነው፡፡

“ከእማዬ ጋር የነበረን ቅርበት ግን የአካል ብቻ ሳይሆን የነፍስ ትስስርና የመንፈስ ቁርኝትም እንደነበረው ይሰማኛል፡፡ በራዕይና በሥነ ምግባር፣ በሀገርና በወገን ፍቅር፣ በክብርና በደግነት፣ በሥርዓትና በቅንነት እንዲሁም በትህትናና በአትንኩኝ ባይነት ሚዛናዊ ሕይወት ኖሮኝ እንዳድግ በልጅነት ዕድሜዬ ማግኘት ከሚገባኝ እንክብካቤ አንዱንም አላስቀረችብኝም” (ገጽ፣ 178)።

“አባቴ ሼህ አሕመድ አሊና እማዬ” ይላሉ  ዐቢይ (ዶ/ር) በመጽሐፋቸው፣ “እሷ እሱ ተብሎ ሊለይ በማይችል የወላጅ ፍቅር የልጅነት ዕድሜዬን ልዩ አድርገው ነው ያሳደጉኝ፡፡ አባቴ ሲበዛ ትጉህ ሰራተኛ ነበሩ፡፡ ንግግር ላይ እምብዛም ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜያቸውን በሥራና በዝምታ ነበር የሚያሳልፉት” ሲሉ (ገጽ፣ 178) አስፍረዋል፡፡

አዲስ መንገድ ፍለጋ

‘የመደመር መንገድ’ መጽሐፍ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥን በአመጻና በጠመንጃ አፈሙዝ ታግዞ ለማምጣት መሞከርን እንጂ በሰላማዊ ትግል ለውጥ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ደካማ መሆኑን ይተቻል፡፡ በሌሎች ሀገሮች እንደታዩት የሰላማዊ ትግል አራማጆች፣ ኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል በማድረግ፣ በትግላቸው ተጨባጭ ውጤት ማምጣት የቻሉ ግለሰቦች ብዙም እንዳላፈራች መጽሐፉ ያብራራል፡፡

ነገር ግን በሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጣት ይቻላል በማለት የወጡ ጥቂት ቆራጥ ታጋዮች ቢኖሩም፣ ብዙሃኑ ሃሳባቸውንና ዓላማቸውን ሲከተል አይታይም ሲል መጽሐፉ ይተቻል፡፡ ይኼም ሆኖ ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም በሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል ጽኑ አቋም ያላቸው ኢትዮጵያውያንን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስም ጠቅሰው ዘርዝረዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም፣ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ዕውቁ የመኢሶን መሪ የነበረው ሃይሌ ፊዳ፣ በደርግ ጊዜ በግፍ የተገደሉትን ቄስ ጉዲና ቱምሳን እንደ አብነት ጠቅሰዋል። እግረመንገዳቸውን፣ “ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግናና ነጻነት እንድትገሰግስ ብዙ መስፍን ወልደ ማርያሞችና አያሌ ብርቱካን ሚደቅሳዎች ያስፈልጓታል” ሲሉ (ገጽ፣ 75) ላይ አድናቆት ችረዋቸዋል፡፡

በመጽሐፉ ውስጥ ሌላው ትኩረት ያገኘው ጉዳይ የህዝብና የመንግስትን ግንኙነት ይመለከታል፡፡ ጭብጡ እጅግ ወሳኝ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ውይይትም ሆነ ክርክር ሲደረግበት ግን አይስተዋልም። ነገር ግን ርዕሰ-ጉዳዩ በአንድ ሀገር የፖለቲካና ኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ ትልቅ ስፍራ መውሰድ ያለበት ነው። በ‘የመደመር መንገድ’ ውስጥ ይህንኑ በሚመለከት የሰፈረው ሃሳብ እንዲህ ይነበባል፤

“በነዋሪው ሕዝብና በመንግስት መካከል የነበረው የሆድና ጀርባ ግንኙነት ጨቅላ ጭንቅላቴን ዘወትር ወጥሮ የያዘ ጉዳይ ነበር፡፡ የሃይማኖት ልዩነትና የብሄር ማንነት ጌጥና ውበት እንጂ የግጭት ምክንያት ባልሆነበት በሻሻ ለምንድ ነው በመንግስትና በማህበረሰቡ መካከል ይሄንን ያህል የጥላቻና የፍርሃት ግንብ ሊቆም የቻለው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ላገኝለት አልቻልኩም” (ገጽ፣ 185) ሲሉ አስፍረዋል፡፡

“በመንግስትና በዜጎች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሰምር ፖለቲካዊ ዐቅም ብቻውን በቂ አለመሆኑን፤ የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልብ ትርታ ማዳመጥና የመደመርን አንድነታዊና ትስስራዊ ፍልስፍና መጠቀም የላቀ ድርሻ ያለው መሆኑን በጥልቅ የተማርኩት ከዚህ ጊዜ [ከልጅነቴ] አንስቶ ነበር” በማለት (ገጽ፣ 187) የመደመር እሳቤ እንዴት እንደተጸነሰ በመጽሐፋቸው ከትበዋል፡፡

በ‘የመደመር መንገድ’ ውስጥ በተለይ ከትናንት የተወረሱ መልከ-ጥፉ የፖለቲካ ባህሎች በፖለቲካዊ ከባቢ ላይ ጥላ ማጥላታቸው ተተንትኗል፡፡ በፖለቲካው ከባቢ ላይ የሚስተዋለው ጥላቻና መልከ-ጥፉ የፖለቲካ ባህል፣ “…ባለፉት ሃምሳና ስድሳ ዓመታት በተቀበልናቸው ትርክቶች፣ በተሰበኩልን ርዕዮተ ዓለሞች፣ በተቀነቀኑልን ሐሳቦች፣ በነፈሱብን የውዥንብር ነፋሶች ምክንያት የተገነባ ነው፡፡ ችግራችን ተፈጥሯችን፣ ባህላችን፣ ቋንቋችንና ብሄራችን ያመጣው አይደለም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ለነዚህ ሁሉ ሺህ ዓመታት ጸንታ አትኖርም ነበር፡፡ ሀገራችንን መሠረት ሆኖ የተሸከማትና ያኖራት የታችኛው መዋቅሯ ነው፡፡ እኔም ከልጅነቴ በበሻሻ ሳየው የኖርኩት የታችኛውን መዋቅራችንን ነው። ላይኛው መዋቅራችን እንደተደራቢ በግድግዳው የተለሰነ ነው፡፡ በትምህርት፣ በውይይት፣ በተሻለ የፖለቲካ ስርዓት፣ በተሻለ ሐሳብና ትርክት ልንቀይረው ግን እንችላለን” ሲል መደመር መጽሐፍ፤ በተለይ ስለ ሀገራዊ ትርክት አስፈላጊነት (ገጽ፣ 193) ያትታል፡፡

በመጽሐፉ ውስጥ ‘ርዕዮተ ዓለም ወይስ ርዕዮተ ኢትዮጵያ?’ በሚለው ምዕራፍ ስር የቀረበው ጉዳይ በጣም ሳቢና አከራካሪ ነው፡፡ “በሀገራችን፣ ርዕዮተ ዓለም ሳታውቀው የምታውቀው፣ ሳይገባህ የምትሞትለት ክፉ መንፈስ ሆኖ ቆይቷል፡፡…ርዕዮተ ዓለም ከሀገር በታች እንጅ ከሀገር በላይ አለመሆኑ ገና ሙሉ በሙሉ አልገባንም፡፡” ሲሉ ( ገጽ፣ 351) አስፍረዋል፡፡

“እንደ አለመታደል ሆኖ በዘመናዊው የፖለቲካ መሥመር ለሀገራችን መፍትሄ እንዲሰጥ ምርኩዝ ያደረግነው ርዕዮተ ዓለም በራሳችን ሀገር በቀል ዕሴት ላይ ተመስርቶ ሳይሆን አውሮፓዊ መንገድን የተከተለ ነበር፡፡ ይኽ ደግሞ ችግራችንን ከመፍታት ይልቅ አዳዲስ ችግሮችን እየፈጠረብን መጣ” (ገጽ፣ 370)፤ በማለት ከውጭ የሚቀዱ ርዕዮተ-ዓለማዊ እሳቤዎች የራሳቸው የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡ የዚህ መፍትሄ ደግሞ እንደ መደመር ሀገር በቀል እሴቶች ላይ የተመሰረተ ርዕዮት አስፈላጊ መሆኑንም ያሰምሩበታል፡፡

በአጠቃላይ መጽሐፉ ሀገር እየመሩ ባሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የተጻፈ በመሆኑ መጽሐፉን ማንበብ እጅግ ጠቃሚ ነው። ‘የመደመር መንገድ’ ማንበብ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ምን አይነት አረዳድ አላቸው? ሀገሪቱ ያለፉት ሃምሳ ዓመታትን የሄደችባቸውን መንገዶች እንዴት ነው የሚገነዘቡት? የመደመር እሳቤ ዋነኛ ማጠንጠኛው ምንድነው? ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደ ግለሰብ ምን አይነት ሰብዕና አላቸው? የሚለውን ጉዳይ ይበልጥ ለመረዳት ያስችላል፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review