ዶናልድ ትራምፕ፣ ዓለም አቀፍ ገበያዎች ውድቀት እያሳዩ መሆናቸውን ተከትሎ ቻይና በአጸፋ የጣለችውን የ34 በመቶ ቀረጥ የማታነሳ ከሆነ፣ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የ50 በመቶ ተጨማሪ ቀረጥ እንደሚጥሉ ዝተዋል።
ባለፈው ሳምንት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሁሉም የአሜሪካ የንግድ ሸሪኮች ላይ በትንሹ የ10 በመቶ ቀረጥ መጣላቸውን ተከትሎ፣ ቤጂንግ በአጸፋው ወደ ቻይና በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የ34 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ወስናለች።
በዚህም የተነሳ ትራምፕ፣ ቻይና እስከ ማክሰኞ ድረስ እርምጃዋን እንድታነሳ አሊያም የ50 በመቶ ቀረጥ እንድትጋፈጥ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የቻይና የንግድ ሚኒስቴር በምላሹ፣ “በስህተት ላይ ሌላ ስህተት” በማለት የአሜሪካን የማስጠንቀቂያ መልዕክት ፈጽሞ እንደማይቀበል ገልጿል።
ትራምፕ በዛቱት መሠረት እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ፣ የአሜሪካ ኩባንያዎች በመጋቢት ወር ከተጣለባቸው የ20 በመቶ ቀረጥ እና ባለፈው ሳምንት ከተጨመረው የ34 በመቶ ቀረጥ ጋር ተዳምሮ ቻይና በምታስገባቸው ሸቀጦች በአጠቃላይ የ104 በመቶ ቀረጥ ሊገጥማቸው እንደሚችል አክሏል።
ይህም በሁለቱ የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ጦርነት ሊያጠነክር ይችላል የሚል ስጋትን አጭሯል።
ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ፣ ቀረጥን በተመለከተ ከቻይና የሚመጡ የእንነጋገር ጥያቄዎች በሙሉ ውድቅ እንደሚደረጉ ጠቁመዋል፡፡
ከተጨማሪ ቀረጥ ጋር በተያያዘ የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ የሚሞክር የትኛውም ሀገር ለሌላ ከፍ ያለ ተጨማሪ ቀረጥ እንደሚጋለጥ መዛታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ