ከተጀመረ 128 ዓመታትን ያስቆጠረው እና የፕላቲኒየም ደረጃ የተሰጠው የቦስተን ማራቶን እሁድ ሌሊት በ30 ሺ ሯጮች መካከል ይካሄዳል፡፡
በሁለቱም ጾታዎች የኢትዮጵያ እና ኬንያውያን አትሌቶች ፉክክር ይጠበቃል፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በየዓመቱ በሚያዝያ ወር ሶስተኛው እሁድ የሚካሄደው የቦስተን ማራቶን ዘንድሮም የዓለማችን ስመ ጥር አትሌቶች ይፋለሙበታል፡፡
ቦስተን በመጪው መስከረም ወር በጃፓን ቶኪዮ ለሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ሚኒማ ከሚያዝባቸው ውድድሮች አንዱ ነው፡፡ የሴቶች አሸናፊነቱ ከኢትዮጵያ የሚወጣ አይመስልም የሚሉ ግምቶች ተበራክተዋል፡፡
የ2022 የለንደን ማራቶን አሸናፊዋ ያለምዘርፍ የኋላው ቀዳሚዋ ግምት ያገኘች አትሌት ናት፡፡ የ2022ቱ ሃምበርግና የባለፈው ዓመቱ አምስተርዳም ማራቶን አሸናፊዋ ያለምዘርፍ እሁድ የምትጠበቅ አትሌት ናት፡፡ ያለምዘርፍ 2 ሰዓት ከ16 ደቂቃ ከ52 ሰከንድ ይዛ ከአማኔ በሪሶ በመቀጠል ከቦስተን ተሳታፊዎች ሁለተኛዋ ፈጣን ሰዓት ያላት አትሌት ናት፡፡
የቡዳፔስቱ ዓለም ሻምፒዮና አሸናፊዋ አማኔ በሪሶ ሌላዋ የምትጠበቅ አትሌት ናት፡፡ አማኔ በ2022ቱ የቫሌንሲያ ማራቶን ያስመዘገበችው 2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ የዓለማችን የምንጊዜውም ሶስተኛው እንዲሁም ከቦስተን ተሳታፊዎች ቀዳሚዋ አድርጓታል፡፡
ያለፉትን ሁለት የቦስተን ማራቶኖች ያሸነፈችው ሄለን ኦብሪ ሌላው ተጠባቂ አትሌት ናት፡፡ በትራክ ውድድሮች ነግሳ ፊቷን ወደ ማራቶን ካዞረችም በኋላ ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈች የምትገኘው ኦብሪ ቦስተን ላይ ሃትሪክ ለመስራት የምትሮጥ አትሌት ናት፡፡ ራህማ ቱሳና ቡዜ ድሪባን ጨምሮ አንጋፋው ኢድና ኪፕላጋት እንዲሁም አሜሪካዊቷ ኬይራ ዲ አማቶ ሌሎች ቦስተን ላይ የሚሮጡ አትሌቶች ናቸው፡፡
በወንዶቹ የባለፈው ዓመት አሸናፊው ሲሳይ ለማ ከተወዳዳሪዎች ቀዳሚውን ከዓለም ደግሞ አራተኛውን ፈጣን ሰዓት ይዞ ቦስተን ላይ የሚጠበቅ አትሌት ነው፡፡ የ2021 ለንደን ማራቶን አሸናፊው እና የ2023ቱን የቫሌንሲያ ማራቶን ሲያሸንፍ የዓለማችን አራተኛውን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው ሲሳይ፤ ከኬንያውያን አትሌቶች ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል፡፡
የ2023 እና 2022 ቦስተን ማራቶን አሸናፊው ኬንያዊ ኢቫንስ ቺቤት ቀዳሚው ነው፡፡ የማራቶን ስፔሻሊስት እየተባለ የሚጠራው ቺቤት ቦስተን ላይ ሃትሪክ ለመስራት የሚጠበቅ አትሌት ነው፡፡ የኒው ዮርክ፣ ቦስተን፣ ቫሌንሲያና ቦነስ አይረስ ማራቶን አሸናፊው ቺቤት ከቦስተን ተሳታፊዎች ሶስተኛው ፈጣን ያለው አትሌት ነው፡፡
የቺካጎ ማራቶን አሸናፊው ጆን ኮሪርና ዳንኤል ማቴኮ ከኬንያ እንዲሁም የቡዳፔስቱ የዓለም ሻምፒዮና አሸናፊው ቪክቶር ኪፕላንጋት ከኡጋንዳ የሲሳይ ለማ ዋነኛ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
የመጀመሪያ ማራቶኑን የሚሮጠው የአምስት ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮና ቀድሞ አሸናፊ ሙክታር ኢድሪስ እንዲሁም የ2024ቱን የበርሊን ማራቶን በሶስተኛነት ሲያጠናቅቅ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ያስመዘገበው ኃይማኖት አለው፣ ቦስተንን ሁለት ጊዜ ያሸነፈው ሌሊሳ ዴሲሳ ብሎም የበርሊን ማራቶንን በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ሳይብሪያን ኮቱት ሌሎች ቦስተን ላይ የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው፡፡
በታምራት አበራ