ኢምብሬር የተባለው የብራዚል የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ በተለያዩ የአቪዬሽን ዘርፎች መሰማራት እንደሚፈልግ ገለፀ

You are currently viewing ኢምብሬር የተባለው የብራዚል የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ በተለያዩ የአቪዬሽን ዘርፎች መሰማራት እንደሚፈልግ ገለፀ

AMN – ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶ/ር ዓለሙ ስሜ ዛሬ የብራዚል ምክትል አምባሳደር ጃክሰን ሊማን ጨምሮ የኩባንያው የስራ ኃላፊዎችን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

መንግስት ለአቪዬሽን ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ በውይይታቸው ወቅት አንስተዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከዓለም ጋር በማገናኘት የአህጉራችን ኩራት እንደሆነ ማስቀጠል ተችሏል ብለዋል፡፡

በአቪዬሽን ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ የግል ኦፕሬተሮች መኖራቸውን ጠቁመው የውጭ ባለሃብቶች ጭምር ሊሳተፉ የሚችሉባቸው አዋጭ የሆኑ የኢንቨስትመንት አማራጮች መለየታቸውን አክለዋል፡፡

የአውሮፕላን ጥገና እና የአውሮፕላን አካል የማምረት አማራጮች አዋጭ የሆኑ ዘርፎች መሆናቸውን ሚኒስትሩ ለአብነት አንስተዋል፡፡

የኩባንያው ተወካዮች በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለአቪዬሽን የሰጠችውን ትኩረት በመመልከት በተለያዩ ዘርፎች መሰማራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

የአውሮፕላን ጥገና፣ የአውሮፕላን አካላት ምርትና የስልጠና መስኮች ቀዳሚ የትብብር ፍላጎቶቻቸው እንደሆኑ በማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ለሀገር ውስጥ በረራ የሚያገለግሉትን አውሮፕላኖችን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከፍላጎት ባሟላ መልኩ ማቅረብ እንደሚችሉና ከአየር መንገዱ ጋርም በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ አንስተዋል፡፡

ሚኒስትር ዶ/ር ዓለሙ ስሜ የኢትዮጵያን የአየር ትራንስፖርት ማዕከልነት ከፍ ሊያደርግ የሚችለውና በቢሾፍቱ አካባቢ ሊገነባ የታሰበው ግዙፍና ዘመናዊ የአየር ማረፊያ ስራ ሲጀምር የአቪዬሽን ዘርፉን ትኩረት የሚስብ ይሆናል ብለዋል፡፡

ኢምብሬር ከተባለው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ጋር በጋራ ለመስራትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግም ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ኢምብሬር የተባለው የብራዚል የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ለህዝብም ሆነ ለጭነት አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ዓይነት አውሮፕላኖችን የሚያመርት መሆኑን ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review