ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለመጎብኘት ሮቤ ከተማ ገብተዋል፡፡
ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ በርካታ የተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦች መገኛ ሀገር ናት፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር በሀገሪቱ የሚገኙ ባህላዊና ተፈጥሮአዊ መስህቦችን የማልማት፣ የመጠበቅና የመንከባከብ ስራ ያከናውናል።
መስህቦችን ለመላው ዓለም በማስተዋወቅ ሀገሪቱ ከዘርፉ ከፍተኛ ገቢ እንድታገኝ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮች የኢትዮጵያን መስህቦች ለመላው ዓለም እንዲያስተዋውቁ ለማድረግ የተለያዩ መርሃ ግብሮች መዘጋጀታቸው ተገልጿል።
በዚህም መሰረት 20 የውጭ ሀገራት አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትን የያዘ ሉዑክ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለመጎብኘት በዛሬው ዕለት ሮቤ ከተማ ገብቷል።
አምባሳደሮቹና ዲፕሎማቶቹ ባሌ ሮቢ ሲገቡ የአካባቢው አስተዳደር አመራሮችና ህብረተሰቡ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም(ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው ዓለም አቀፍ ቅርሶች መካከል አንዱ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ነው፡፡
በ1962 ዓ.ም እንደተመሰረተ የሚነገርለት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተለያዩ ብርቅዬ እንስሳት እና እጽዋት መገኛ እንዲሁም ውብ የተፈጥሮ ገጽታ ያለው ፓርክ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡