ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የዓለም ባንክ ግሩፕ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሂዷል።
በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢርድ ጋር ተወያይቷል።
ልዑኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) እና ሌሎች አባላትን ያካተተ ነው።
ውይይቱ እስከ አሁን በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተገኙ ውጤቶች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል።
የዓለም ባንክ ግሩፕ ለኢትዮጵያ ልማት አጀንዳ፣ ለቀጣናዊ ልማት እና ትስስር መጎልበት የሚያግዙ ኢኒሼቲቮች ላይም ምክክር ተደርጓል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የልማት ጥረቶች እና የሪፎርም አጀንዳ እያደረገ ላለው የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ሪፎርሙ ኢኮኖሚውን ለማጠናከር እና ለማዘመን፣ አዲስ የእድገት እድሎችን ለመክፈት፣ የግሉ ዘርፍ ስራ እድል ፈጠራን ጨምሮ ያለውን የኢኮኖሚ ተሳትፎ ለማጠናከር እና የኢትዮጵያውያንን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችል ነውም ብለዋል።
የዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢርድ ኢትዮጵያ ለሪፎርም ማዕቀፉ ትግበራ ያሳየችውን ቁርጠኝነት እና ዓለም አቀፍ ጫናዎችን በመቋቋም የማክሮ ኢኮኖሚ ቁልፍ ግቦችን በማሳካት ያከናወነችውን ስራ አድንቀዋል።
መንግስት መልካም ጅማሮ የታየበትን የሪፎርም ፕሮግራም እንዲሁም በሀገር አቀፍና ክልል አቀፍ ደረጃ ቁልፍ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ እያከናወነ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንዲጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሁሉም አጋር አካላት የኢትዮጵያን እድገት እና ዘላቂ ልማት የሚያስቀጥሉ ስራዎችን እንዲደግፉ ጥሪ መቅረቡን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።