በመዲናዋ የተጀመረውን የኮሪደር ልማት በሁሉም አካባቢዎች ለማዳረስ በቅደም ተከተል እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
ከንቲዋ ይህን ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ኛ አመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
ለውጡን ተከትሎ ለህዝባችን ቃል ገብተን እና ራዕያችን አድርገን የተነሳነው አዲስ አበባን እንደስሟ ውብና ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ የህዝቡ ጥያቄ መሰረታዊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ በተከናወነባቸው አካባቢዎች በርካታ ጥቅሞች እንደተገኙና በዚህም የመዲናዋ ነዋሪዎች ደስተኛ መሆናቸውንም ከንቲባ አዳነች አመልክተዋል፡፡
አዲስ አበባም እንደስሟ ውብ፣ለነዋሪዎቿ የምትመችና በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ ከተማ እንድትሆን የኮሪደር ልማቱ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል፡፡
በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የአረንጓዴ ቦታዎች፣ የአውቶብስና የታክሲ መጫኛና ማውረጃ ፌርማታዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች እና ሌሎችንም ያካተተው የኮሪደር ልማት ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታን እያስገኘ እንደሚገኝም ከንቲባዋ አመላክተዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ባልተዳረሰባቸው የመዲናችን አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችንም የዚህ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በቅደም ተከተል እየስራን ነው ብለዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ያረጁና በመፈራረስ ላይ የሚገኙ ቤቶችን አፍርሶ ለመገንባ ጊዜና ገንዘብ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች፣ ህብረተሰቡ እንደተለመደው በትዕግስት እንዲጠብቅና ለስራውም ተሳታፊ እንዲሆን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳስበዋል፡፡