የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ማደጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 3ኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ መርቀው ከፍተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በመርሐግብሩ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ማደጉን ተናግረዋል፡፡
ለአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ያነሱት ሚኒስትሩ በዚህም ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ነው ያሉት፡፡
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው እና በ10 ዓመቱ የልማት አቅድ የተያዙ የዘርፉ ግቦችም እየተሳኩ መሆኑን አውስተዋል።
በንቅናቄው የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያን በአምራች ኢንዱስትሪ የበለጸገች ሀገር የማድረግ ህልማችን ሩቅ እንዳልሆነ ያመላከተ ነው ሲሉም ገልጸዋል ሚኒስትሩ።
በቀጣይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኙ ውጤቶችን ማስቀጠል እና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ ማስገባት ትኩረት እንደተሰጠው አስታውቀዋል፡፡