በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ከ815 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ

You are currently viewing በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ከ815 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ

ሰኔ 23/2017 ዓ.ም

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገቢዎች ሚኒስቴር የገቢው ዘርፍ የ2017 በጀት አመት የ11ወራት አፈፃፀምን ገምግሟል።

የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ከሀገር ውስጥ ታክስ እና ከወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ ከ900 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል።

እስካሁን ባሉት የበጀት ዓመቱ 11 ወራት 815 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉንም ነው ያብራሩት።

በወጪና ገቢ ኮንትሮባንድ ላይ በተደረገው የቁጥጥር ስራ 19 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉንም ተናግረዋል።

የሚኒስቴሩንና የጉሙሩክ ኮሚሽንን አሰራሮች የሚያዘምኑ የተለያዩ ዲጂታል የቴክኖሎጂ አሰራሮችን ማልማትና ወደስራ እንዲገባ መደረጉንም ገልፀዋል።

የስነምግባር ጉድለት የታየባቸው 405 ሰራተኞች ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ስንብት የሚደርስ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ በወንጀል እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ መሰራቱንም አስረድተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በቀጣይ በጀት ዓመት ከዘንድሮ ብልጫ ያለው ገቢ ለመሰብሰብ በመታቀዱ ይህን ለማሳካት እንዲሁም የታክስ ገቢ እድገትን ለማረጋገጥ ምን እየተሰራ ነው የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ልዩ የደረሰኝ ህትመት ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ችግርና የኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድረው ህገወጥ ኬላዎች ላይ ምን እየተሰራ ነው የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ሚኒስትሯ በሰጡት ማብራሪያ በበጀት ዓመቱ ቀጣይነት ያለውና የአገር ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የተያዘውን የገቢ እቅድ ለማሳካት እቅዱ በተገቢው ትንተና ላይ ተመስርቶ መሰራቱንና የዲጂታል አማራጮችን መተግበር አስቻይ ሁኔታ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑንም ተናግረዋል።

የታክስ አስተዳደር ውጤታማነትን የሚያሳድጉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ነው ያብራሩት።

በደረሰኝ የሚስተዋሉ ማጭበርበሮችን ለመከታተል እንዲያመች በኪውአር ኮድ(QR CODE) የተደገፈ ደረሰኝ ወደስራ ለማስገባት ከአሳታሚ ድርጅት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

700 ሺህ የእጅ በእጅ ሽያጭ ደረሰኝ ህትመት ለማድረግ ታስቦ ወደ ስራ ቢገባም ፍላጎቱ በሶስት እጥፍ ያደገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚሁ መሰረት የአሳታሚውን ድርጅት አቅም የማሳደግ ስራ እየተሰራ ከመሆኑ ባለፈ ወደ ዲጂታል የደረሰኝ አገልግሎት ለመግባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የጉሙሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አዝዘው ጫኔ በበኩላቸው ህገወጥ ኬላዎች በወጭና ገቢ ንግድ ስርዓቱ እንዲሁም በሀገራዊ ገቢ ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለማስቀረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስገንዘባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review