AMN- የካቲት 19/2018 ዓ.ም
ለዓመታት የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ለብዙ እናቶች የገቢ ምንጭ ብቻ ሳይሆኑ የፈተና አውድማም ነበሩ።
በጋው በአቧራና በንፋስ፣ ክረምቱ ደግሞ በጭቃና በዝናብ እየታጀበ እናቶችን ሲፈትናቸው ቆይቷል።
ዛሬ ግን ያ ታሪክ ተቀይሮ እናቶች በደስታ “ገነት ላይ ነው የተቀመጥነው” የሚሉበት አዲስ ምዕራፍ ተጀምሯል።
በጎዳና ላይ ጉሊት በመሸጥ ይተዳደሩ የነበሩት ወይዘሮ አደቦ በርታ እና ወይዘሮ በህሪያ አበሻ በጎዳና ላይ ንግድ ከባድ ፈተናዎች ሲያሳልፉ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡
ፀሀይ እና ዝናብ እየተፈራረቁባቸው በአቧራና በቆሻሻ መካከል በመሸጥ በሜዳ ላይ ለከፍተኛ እንግልት ይጋለጡ እንደነበር ያነሳሉ።
የመስሪያ ቦታቸው ጊዜያዊ በመሆኑ በማንኛውም ሰዓት ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ በማሰብ የስራ ዋስትና የማጣት ስጋትም እነደነበረባቸው ይገልፃሉ።
በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእነዚህን እና የሌሎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እናቶችን ህይወት ለመለወጥ በልደታ ክፍለ ከተማ መካኒሳ አካባቢ ዘመናዊ የጉሊት የገበያ ማዕከል ገንብቶ አስመርቋል።

ሻጮች ከፀሀይና ከዝናብ ተከልለው በንጽህና መስራት የሚያስችላቸው ንጹህና ምቹ ሼዶችን በማመቻቸት ምርቶች እንደ አይነታቸው ሽሮና ቅመማቅመም ተለይተው ጽዳት ባለው ሁኔታ መቅረብ ችለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የሚሸጠው ነገር የሚበላ የሚጠጣ በመሆኑ እናቶች ቆሻሻ ላይ ተቀምጠው መሸጥ የለባቸውም በሚል፣ ከጎዳና ላይ በማንሳት ሼድ በመሥራት ቅድሚያ ለተነሺዎች በመስጠት እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የገበያ ማዕከሉም እናቶች ያለምንም ስጋት እንዲነግዱ በማድረግ የገቢ አቅማቸውን ለማሳደግ ዓላማ ያደረገ ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።
አዲሱ ማዕከል ለእናቶቹ የሰጣቸው እፎይታ ከንግድ ባለፈ ሥነ-ልቦናዊ ሰላምን ጭምር ነው።
ወይዘሮ አደቡ በርታ እና ወይዘሮ ባህርያ አበሻን የመሰሉ እናቶች ዛሬ ሸቀጦቻቸውን በዘመናዊ መልክ ለተጠቃሚዎች እያቀረቡ ይገኛሉ።
ማዕከሉ ለሸማቾችም ቢሆን ሩቅ ሳይሄዱ በአቅራቢያው ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኙ ትልቅ እድል የፈጠረ ነው።
ይህ ዘመናዊ የጉሊት የገበያ ማዕከል የእናቶችን ድካም በብዙ የቀነሰ መሆኑን በማዕከሉ የመሥራት ዕድል ያገኙት እናቶች ተናግረዋል፡፡
በታምራት ቢሻው