በአዲስ አበባ ከተማ 4.2 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ

You are currently viewing በአዲስ አበባ ከተማ 4.2 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ

AMN- ሰኔ 24/2017 ዓ.ም

በ7ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ ከተማ 4.2 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተደራጀ አግባብ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳት እና አባቶች ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር በቦሌ ክፍለ ከተማ በቪአይፒ ተርሚናል አካባቢ ችግኝ ተክለዋል።

በአዲስ አበባ ደረጃ የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር መጀመሩን የተናገሩት ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የችግኝ ተከላ ስራው ነዋሪዎች በስፋት እየተሳተፉበት ቀጥሏል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ፓትርያሪክን ጨምሮ የቤተ ክርስትያኗ አባቶች በችግኝ ተከላው ላይ መሳተፋቸው አርዓያነት ያለው ተግባር እንደሆነም አንስተዋል፡፡

የቤተ ክርስትያኗ ምዕመናን እና ሌሎች የእምነት ተቋማት እንዲሁም ሌላው ነዋሪ በተደራጀ አግባብ በቀጣይነት በችግኝ ተከላው ላይ በመሳተፍ ዕቅዱን ለማሳካት እንዲረባረብም አቶ ጃንጥራር አባይ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ በበኩላቸው፣ እጽዋትን መትከል እና መንከባከብ በቤተ ክርስትያን አስተምህሮ የሚደገፍ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ምዕመናን በችግኝ ተከላው በስፋት ሊሳተፉ እና የተተከሉትንም ሊንከባከቡ ይገባል ብለዋል።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review