በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 6 ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር፣ የደን ሽፍንን በማሳደግ ረገድ አመርቂ ስኬት መመዝገብ መቻሉን በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ገልጸዋል።
አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ለሰው ልጅ ጠቃሚ ከመሆኑም ባለፈ ጠፍተው እና ተሰደው የነበሩ የዱር እንሰሳት ወደ ቀደመው ሕይወታቸው እንዲመለሱ መደረጉንም ተናግረዋል።
በአፈር መሸርሸር ምክንያት የሚከሰተውን ችግሮች ከመቅረፍ ባለፈ፣ የስንዴ ልመና ማስቀረት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ሲሉም አቶ አዲሱ ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኤሊያስ ከድር በበኩላቸው፣ ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ከገጠር ወደ ከተማ ያለውን ፍልሰት መቀነስ እንደተቻለም ተናግረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭ ተፈጥሮን በመንከባከብ ለቀጣይዩ ትውልድ ሀውልት የሚሆን ስራ ተሰርቷል ሲሉም ምክትል ቢሮ ኃፊው አክለዋል።
በኦሮሚያ ክልል 7ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወንጪ ወረዳ በሰንኮሌ ተራራ ተካሄዷል።
በዳንኤል መላኩ