ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተባብረን ማደግ ነው የምንፈልገው የእኛን ፍላጎት ማክበርም ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናገሩ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በስብሰባው የመንግስትን የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃጸም አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን የሰላምና የልማት ትብብር ማስቀጠል ፍላጎት አላት ብለዋል።
ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የጎረቤት ሀገራት በጎ ምላሽ ሊሰጡ ይገባልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሰላም የአካባቢው ሰላም ነው ያሉት ጠቅላይ መሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ከሌለ የአካባቢ ሀገራትም ተጎጂ ይሆናሉ ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአካባቢው ሀገራት ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ ማድረግ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ናት የጎረቤቶቿንም ሉዓላዊነት ታከብራለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመኖርም የባሕር በር ፍላጎቷን ሰጥቶ በመቀበል መርሕ ሊያከብሩ እንደሚገባ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ 130 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት፣ የዘመነ ወታደርና ቴክኖሎጂ የታጠቀች ሀገር ብትሆንም በምንም አይነት ውጊያን አማራጭ አታደርግም ሲሉ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ከሁሉም ወገን ጋር ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት ለማስቀጠል ፍላጎት መኖሩንና ከሁሉም ወንድሞቻችን ጋር በሰላም መኖር እንፈልጋለን ብለዋል።
ነገር ግን በሰላም የማያኖር ጉዳይ ሲኖር እራሳችንን ለመከላከል እንሞክራለን ሲሉም ገልጸዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።