AMN – የካቲት 15/2018 ዓ.ም
አርሰናል በ199ኛው የሰሜን ለንደን ደርቢ ቶተንሃም ሆትስፐርስን 4ለ1 አሸነፈ።
በሁለት ተከታታይ ጨዋታ ነጥብ በመጣሉ ጫና ውስጥ ገብቶ የነበረው አርሰናል ሙሉ ብልጫ በመውሰድ ነው ወሳኝ ድሉን ያሳካው።
በጨዋታው ኤብሪቼ ኤዜ ሁለቱን የመድፈኞቹን ግብ በስሙ አስመዝግቧል። እንግሊዛዊው ተጫዋች በመጀመሪያው ዙር የደርቢው ጨዋታ ኤምሬትስ ላይ አርሰናል 4ለ1 ሲያሸንፍ ሀትሪክ መስራቱ ይታወሳል።
ሌሎቹን የአርሰናል ግቦች ስውዲናዊው አጥቂ ቪክቶር ዮኬሬሽ ማስቆጠር ችሏል። አጥቂው በአርሰናል መለያ ያከናወነው ድንቅ ጨዋታ ከመሆኑም በላይ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።

በአዲሱ አሰልጣኝ ኢጎር ቱዶር እየተመራ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ቶተንሃም በራንዳል ኮሎ ሙአኒ ግብ ቢያገኝም ልዩነት መፍጠር አልቻለም።
አስቸጋሪ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ቶተንሃም ከወራጅ ቀጠናው በአራት ነጥብ ብቻ ርቆ በ29 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ 2026 ከገባ አንድም የሊግ ጨዋታ አላሸነፈም።
አምስተኛ ተከታታይ የሰሜን ለንደን ደርቢውን ያሸነፈው አርሰናል በአንፃሩ በ61 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል። አንድ ተጨማሪ ጨዋታ ያከናወነው ክለቡ ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት አስፍቷል።
አርሰናል በቀጣይ የፊታችን እሁድ ከቼልሲ ጋር በኤምሬትስ ይጫወታል።
በሸዋንግዛው ግርማ