የ37 ዓመቷ ቻይናዊት ጋኦ ለሌሎች ሰዎች ማስጠንቀቂያ ይሆናል በሚል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፈችው ፎቶ መነገጋገሪያ ሆናለች፡፡
ለ22 ዓመታት የተጠቀመቻቸውን የፊት መዋቢያዎች በአግባቡ ከፊቷ ላይ ባለማፅዳቷ የቆዳ አለርጂ ሆኖባት የፊቷን ገፅታ ቀይሯል፡፡
በልጅነቷ እናቷ ስትዋብ እያየች ያደገችው ጋኦ፣ በሴቶች የፊት መዋቢያ የተሳበችውም ከ15 ዓመቷ ጀምሮ መሆኑን ትናገራለች፡፡
ይሁንና በጧት ፊቷ ላይ የተቀባችውን ሜካፕ ማታ ወደ መኝታዋ ከመመለሷ በፊት በውሃ ብቻ እንደነገሩ የመታጠብ ልምድ ነበራት፡፡
ይህን የምታደርገው ጧት ከእንቅልፌ ስነሳ ዳግም መቀባቴ ላይቀር ምን አደከመኝ በሚል የስንፍና ሀሳብ መሆኑን ገልፃለች፡፡
በማግስቱም ተጨማሪ መዋቢያ ፊቷ ላይ ጨምራ ውሎዋን ትቀጥላለች፡፡ በዚህ መልኩ ላለፉት 22 ዓመታት ተመሳሳይ መንገድ ተከትላለች፡፡
ፊቷ የተቃጠለ ከመምሰሉና እሷነቷን እንኳ ለመለየት አስቸጋሪ ከመሆኑ በፊት አልፎ አልፎ ፊቷ ላይ ብጉር ይታይ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
በወቅቱም የቆዳ ህክምና ባለሙያ ሳታማክር ወደ ውበት ክሊኒክ በማምራት የተጠቀመችው የቆዳ ማሳመሪያ መርፌም ችግሩን እንዳባባሰባት ትናገራለች፡፡
በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡ የቆዳ ህክምና ባለሙያዎች 22 ዓመታት ፊትን በአግባቡ አለማፅዳት በርግጥም ከባድ ነው ብለዋል፡፡
በጋኦ ፊት ላይ እያየን ያለው ነገር እጅግ ውስብስብ ነው፤ ምናልባትም የጠንካራ ምርቶች ድብልቅ፣ በተደጋጋሚ መርፌዎችን መጠቀም እና ለመዋቢያነት የሚውል የስቴሮይድ ንጥረ ነገር አጠቃቀም ችግር በመንስኤነት ሊጠቀስ እንደሚችል ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡
ፎቶዋ ዌቦ በተሰኘው የቻይና ማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ ከተለቀቀ ወዲህ በርካቶች መነጋገሪያ አድርገውታል፡፡
ጋኦ አሁን ላይ የፊት ገጽታዋ መቀየሩን ተከትሎ ከቤት አትወጣም፣ ከሰዎችም ጋር አትገናኝም ሲል ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል፡፡
በማሬ ቃጦ