የመዲናዋ ጎዳናዎች ትናንትና እና ዛሬ

You are currently viewing የመዲናዋ ጎዳናዎች ትናንትና እና ዛሬ

ቀናችንን ስንጀምር “ሰላም አውለኝ፤ ከድንገተኛ ክስተት ታደገኝ” ብሎ እንደየ እምነታችን ፈጣሪን ለምኖ መውጣት መልካም ነው። ይህን ልንል የወደድነው በምክንያት ነው። ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት በማሽከርከር ሙያ ዘርፍ ተሰማርተው ይሰሩ የነበሩት አቶ ቴዎድሮስ ሰለሞን አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሲያሽከረክሩ የገጠማቸውን ሳቅ እየቀደማቸው የተረኩልንን ስንሰማ አባባሉን ልብ እንድንለው ያስገድደናል፡፡

“ከዕለታት በአንዱ ቀን መኪናዬን እያሽከረከርኩ እያለ የተቦረቦረ አስፋልት ውስጥ ገባሁ፡፡ አስፋልቱ ያቆረው ውሃ በጭቃ የተሞላ ስለነበር ታክሲ ስትጠብቅ የነበረችውን የዘነጠች ወጣት ጭቃ አለበሳት፡፡” ሲሉ ገጠመኛቸውን የጀመሩት አቶ ቴዎድሮስ፣ በወቅቱ የወሰዱት እርምጃም እንደ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ድርጊቱን ፈፅሞ በፍጥነት አካባቢውን ጥሎ መሄድ አልነበረም፡፡ ከሁሉም ያስቀደሙት መኪናቸውን ወደ ዳር በማቆም ይቅርታ መጠየቅን ነበር፡፡ ወጣቷን በተፈጠረው ድርጊት ይበልጡኑ እንድትበሳጭ ያደረጋት ምክንያት በወቅቱ ለስራ ቅጥር የቃለ መጠይቅ ፈተና ለመውሰድ ባላት ነገር ዘንጣ እየሄደች እያለች መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ይህ ክስተት እንዴት እንደተፈጠረ አቶ ቴዎድሮስ ሲያስረዱም፤ ወጣቷ ጉዳዩን እንዲህ በቀላሉ ማለፍ ስላልወደደች የተበላሸባትን ልብስ በአዲስ እንዲቀየርላት ነበር  የጠየቀችው፡፡ እርሳቸውም በወቅቱ የነበሩበት ድንጋጤ አይደለም ልብስ ሌላ የሚክሳትን ለማድረግ ፍቃደኛ ነበሩ። ያለችውንም አደረጉላት፡፡ ለስራ ቅጥር የነበራት መጠይቅ እንዴት እንደሆነ ለመስማት ስልክ በመለዋወጥ ነበር የተለያዩት፡፡ ታድያ በሚያናድደው ክስተት የተዋወቁት ግለሰቦች ደጋግመው በመደዋወል ህይወታቸውን ወደ ፍቅር መስመር ቀየሩት፡፡ ቤተሰብ መስርተው በመኖርም ደስተኛ ህይወት እያሳለፉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

“በህይወታችን የሚገጥሙን ጉዳዮች የቱንም ያክል መጥፎ ቢሆኑም እንኳን መልካም ነገር ይዞ እንደሚመጣ ማሰብ ያስፈልጋል” የሚሉን አቶ ቴዎድሮስ የገጠማቸው መጥፎ አጋጣሚ ለመልካም እንደሆነላቸው ሲያስቡ እንደሚደሰቱ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም አዲስ አበባችን ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበራት የመንገድ ስርዓት በርካቶችን ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ የሚያደርግ ነበር፡፡ የመንገድ ጥበት፣ የተጎዱ አስፋልቶች እንዲሁም እግረኛው ከአሽከርካሪ እኩል እየተጋፉ መሄድ እምብዛም አዲስ ባልነበረባት ከተማ የኮሪደር ልማቱ ፍፁም ገፅታዋን በመቀየር አዲስ ገፅታ እንደለገሳት አብራርተዋል፡፡

በተለምዶ ጉርድ ሾላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በእግረኛ መንገድ ሲጓዙ ያገኘናቸው አቶ ዘሪሁን ፃዲቅ፤ አዲስ አበባ ከተማ ላይ መኖር ከጀመሩ በርካታ ጊዜያትን ያስቆጠሩ ሲሆን በስራ እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከተማዋን ጠንቅቀው ያውቋታል። ከዚህ ቀደም በአንዳንድ ዋና ዋና መንገዶች ጭምር አስነዋሪ ብሎም ቀንን የሚረብሽ ተግባር ይፈጸም እንደነበር የእሳቸውን ገጠመኝ በማሳያነት በማጣቀስ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ በውሃ መጠጫ በተለምዶ ሃይላንድ በሚባሉት የፕላስቲክ ውሃ መያዢያዎች ውስጥ ሽንት በመሽናት በመንገድ አስፋልቶች ላይ የሚጥሉ ግለሰቦች አሉ፡፡ ይህንንም ተከትሎ መኪናዎች ሲረግጧቸው ሰው ላይ ይረጫሉ፡፡ በእርሳቸው ላይ የሆነውም ይኸው ነበር፡፡

አቶ ዘሪሁን በአስተያየታቸው፤ የቱንም ያክል ከተሞች ቢፀዱም እንኳን የፀዳ አስተሳሰብን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ “አንድ ሰው የሰራውን ምግብ የሚመገበው በንፁህ የመመገቢያ ሰሃን እንደሆነው ሁሉ ያማሩና ያሸበረቁ መንገዶች ላይ ቆሻሻ መጣልም የእግረኛውን የመንቀሳቀስ መብት እንደ መረበሽ ነው የሚቆጠረው” ብለዋል፡፡ ባደጉ ሀገራት እናየው የነበረውን የሰለጠነ የመንገድ ስርዓት እዚሁ ሀገራችን ላይ ሆኖ ስናየው በእጅጉ አስደስቶናል ብለዋል፡፡

የመንገድ መብራቶች ለአስፋልቶቹ የሰጡት መልካም ድባብ መንፈስን የሚያረጋጋ ብሎም ሰላምን የሚሰጥ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዘሪሁን ከዚህ ቀደም አምሽተው የመስራት ልምድ  ነበራቸው፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ ከስራ ወደ ቤታቸው እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ነበር፡፡ ሌቦች ጨለማን ተገን በማድረግ ስልካቸውን እና በኪሳቸው የነበረውን ገንዘብ የዘረፏቸው። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያነሱት የመንገድ ዳር መብራቶች ባለመኖራቸው ሌቦች ድፍረት እንዲያገኙ አድርጎቸዋል የሚለውን ነው፡፡ አሁን ግን ምሽቱም እንደ ቀን ስለደመቀ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት እና 4፡00 ሰዓት እንቅስቃሴ ቢደረግ ማንም ዞር ብሎ አያይም፡፡ የመንገድ ላይ የደህንነት ካሜራዎች እግረኞች በጥንቃቄ አንዲጓዙ አሽከርካሪዎችም በአግባቡ የትራፊክ ህጎችን ተከትለው እንዲያሽከረክሩ አግዟል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ሰፋፊ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገድ፣ ለአካል ጉዳተኞች የተለየ መንገድ መሰራቱ፣ ሰፋፊ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች መዘጋጀታቸው የትራፊክ አደጋን በመቀነስ በእግረኛው፣ በአሽከርካሪው ብሎም በመንገድ ሃብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ አይነተኛ መፍትሔ ነው ሲሉም አክለዋል።

ወጣት አወቀ አረጋ ይባላል፡፡ በተለምዶ ሲ ኤም ሲ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጀርባ በጭነት አገልግሎት ተሰማርቶ ይሰራል፡፡ “ያደጉ ሀገራት ከተሞቻቸውን መልሰው ያለማሉ፤ ያድሳሉ፡፡ አዲስ አበባም የዚያ በረከት ተቋዳሽ ስትሆን እንደማየት የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ ከዚህ ቀደም መኪናዬን አቁሜ ስሄድ ስፖኪዮ (የሚኪናዬ የጎን መስታወት) ይሰረቅ ነበር፡፡ አሁን ግን ሰፋፊ እና ለማቆም ምቹ የሆኑ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች መኖራቸው እፎይታን ፈጥረውልኛል” ብሏል፡፡

እንደ አንድ አሽከርካሪ ቦሎ ለማደስ የመኪና የቴክኒክ ምርመራ ይካሄዳል። እግር መንገድም ለመንገድ ፈንድ በሚል የተወሰነች ክፍያ ይከፈላል፡፡ ታድያ ይህ  ክፍያ ለተጎዳው መንገድ መጠገኛ የሚውል ነው፡፡ ታድያ ለበርካታ ዓመታት የመንገዶችን ደህንነትን ለማስጠበቅ እምብዛም አልተሰራበትም። አሁን ግን ሰፋፊ የመኪና እንዲሁም የእግረኛ መንገዶች በስፋት ተሰርተዋል። ከዚያም በላይ ከሩቅ ሆነን ብናያቸው ብሎም ጥሩ ጊዜ ብናሳልፍባቸው ብለን ያሰብናቸውን መናፈሻዎች ከደጃፋችን እነሆ መባላችን እጅግ እድለኛ ያስብለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደኔ ያለ በእድሜ ገፋ ያለ አዛውንት መንገድ ሲደክመው የሚያርፍበት፤ ጥሩ የእግር ጉዞ ማድረግ ሲፈልግ ወገቡን አረፍ የሚያደርግበት ስፍራ ያስፈልገዋል የሚሉት ደግሞ አቶ ተሾመ ባልቻ ናቸው። ነዋሪነታቸው ኮተቤ ዜሮ ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን በብዛት የእግር መንገድ ጉዟቸውን የሚያደርጉት ከካራሎ ወደ ሰሚት በሚወስደው መንገድ ከሰዓት ከ11፡00 ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ደከም ሲላቸው በመንገድ ዳር በተዘጋጁ ወንበሮች አረፍ በማለት ከተክሎች የሚያገኙትን መልካም አየር እየሳቡ ጤናቸውን መጠበቅ የእለት ተዕለት ተግባራቸው እንደሆነ ነግረውናል፡፡

በዓለም በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ እንደሚሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ 2023 ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡ ከ50 ሚሊዮን በላይ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሀገሮች ደግሞ ችግሩ የከፋ ነው፡፡ እንደ ሀገርም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከሰተ ያለው የትራፊክ አደጋ መንስኤ ከሆኑት ምክንያቶች ከግንባር ቀደምቶቹ ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል የእግረኛ እና የመኪና አስፋልቶች ጥበት፣ የመኪና አሽከርካሪና ሳይክል የሚነዱ ሰዎች መንገድ አለመለየት፣ የመንገድ ዳር መብራቶች በአግባቡ አገልግሎት አለመስጠት እና የደህንነት ካሜራዎች አለመኖራቸው ችግሩን የከፋ አድርጎት እንደነበር እሙን ነው፡፡ የኮሪደር ልማቱ ዘርፈ ብዙ ትሩፋት ስላለው ደህንነቱን መጠበቅ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል እንላለን፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review