ዩክሬን ከሩሲያ ጋር አዲስ ዙር የሰላም ውይይት ለማድረግ ማቀዷን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ገለጹ።
የተኩስ አቁም እንዲደረስ ሁሉም ነገር መደረግ አለበት ያሉት ዜለንስኪ፣ የዩክሬን ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣን ሩስቴም ኡሜሮቭ፣ በሚቀጥለው ሳምንት በሩሲያ ወገን ከሚቀርቡ ተደራዳሪዎች ጋር ለመገናኘት መወከላቸውን አስታውቀዋል።
በሞስኮ እና በኪዬቭ መካከል በኢስታንቡል የተካሄደው የሁለት ዙር ውይይት እስካሁን የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ባያስችልም፣ የጦር እስረኞችንና የወታደሮችን አስከሬን ለመለዋወጥ ማስቻሉ ይታወሳል።
ዜለንስኪ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ገፅ ለገፅ ለመገናኘት ያላቸውን ዝግጁነት የገለጹ ሲሆን፣ በመሪዎች ደረጃ የሚደረግ ውይይት ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የውይይት ሃሳቡ የመጣው፣ ሩሲያ በዬክሬን ላይ መጠነ ሰፊ የቦምብ ጥቃት ከፈጸመች እና የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፋ ከተገለፀ ከሰዓታት በኋላ መሆኑም ተገልጿል።
ዓርብ እና ቅዳሜ ማታ በተፈጸመ ጥቃት፣ በርካታ ከተሞችን ጨምሮ አስር የዩክሬን ግዛቶች መመታታቸውን ዜለንስኪ ተናግረዋል።
የዩክሬን መከላከያ በበኩሉ፣ በጥቃቱ ከ340 በላይ ፈንጂ እና አውዳሚ ድሮኖች እንዲሁም 35 ክሩዝ እና ባላስቲክ ሚሳኤሎች ጥቅም ላይ ቢውሉም ብዙዎቹ ተመተው መውደቃቸውን ገልጿል፡፡
በብርሃኑ ወርቅነህ