የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለዘላቂ ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ሰራተኞች ዛሬ ሰባተኛ ዙር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄደዋል።
በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ የጎርፍ፣ ድርቅ፣ የአፈር መሸርሸርን ጨምሮ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እንቅፋት የሚሆኑ ሳንካዎችን ፈጥሯል።
ለእነዚህና መሰል ችግሮች ምላሽ ለመስጠት ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተግባራዊ ባደረገችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 40 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም በአፍሪካም ሆነ በዓለም ምሳሌ የሚሆን ውጤት ተገኝቷል ያሉት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ፤ በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን ልማትና ብልጽግና ቀጣይነት የሚያረጋግጡ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን አብራርተዋል።
በአገር ደረጃ የሚተከሉ ችግኞች የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ለግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ነው ያስታወቁት።
ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በስፋት እየተተከሉ መሆኑን ጠቁመው፥ ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘው አገራዊ ግብ እውን እንዲሆን ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
“በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ ዘንድሮ እየተከናወነ ለሚገኘው ሰባተኛ ዙር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ስኬት ሁሉም የበኩሉን አሻራ እንዲያኖር ጥሪ አቅርበዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ፋንታዬ ለገሰ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ መርሃ ግብር ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገር ትሩፋት እየተገኘበት ያለ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አረንጓዴ አሻራ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኩራት መሆኑንም ገልጸዋል።
ችግኞቹን ከመትከል ባሻገር ተንከባክቦ ለውጤት እንዲበቁ ማድረግ ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላዋ የምክር ቤት አባል አምሳል መንግሥቱ ናቸው።