በአዲስ አበባ ከተማ የክረምት ወቅት የኮደርስ ስልጠና መሰጠት መጀመሩ ተገለፀ

You are currently viewing በአዲስ አበባ ከተማ የክረምት ወቅት የኮደርስ ስልጠና መሰጠት መጀመሩ ተገለፀ

‎AMN- ሐምሌ 18 /2017 ዓ. ም

‎በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ 5 ሚሊዮን ዜጎችን የዲጅታል ክህሎት እንዲያገኙ የሚያስችል የኮደርስ ኢኒሼቲቭ እየተተገበረ ይገኛል።

‎ዘንድሮም በተለይም በክረምት ወቅት ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን የኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አወሌ መሀመድ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል።

‎ስልጠናው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና አምራች ሀይል ለመፍጠር እንደሚያግዝ ገልፀው፣ ወጣቱ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል፡፡

‎የዩኒቨርስቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በ77 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የኮደርስ ስልጠና እንዲያገኙ መመቻቸቱን እና ከእነዚህ ውስጥ ስልጠና የጀመሩ መኖራቸውን አስረድተዋል።

‎የኮደርስ ስልጠናው ከስድስት እስከ ስምንት ሳምንት የሚወሰድ ሲሆን በክረምት ወቅት ታዳጊዎችና ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

‎ስልጠናው አራት ኘሮግራሞች ያሉት ሲሆን መሰረታዊ ኘሮግራሚንግ፣ዳታ ሳይንስ፣የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ አንድሮይድ ኘሮግራሚንግ ናቸው።

‎እስከ አሁን ከላይ በተጠቀሱት ኘሮግራሞች መሰረት 237,720 ዜጎች ስልጠናውን ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

‎ለወጣቱ የፈጠራ ስነምህዳር ከመፍጠር አኳያ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ፣ በአለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ የሰው ሀይልን ለመፍጠር እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

‎ከዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት አንፃር ህንድ ለአብነት ያነሱት ሀላፊው፣ ከሶፍትዌር ኢንደስትሪው ለጂዲፒዋ 7 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል። በዚህም 256 ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ ከሶፍት ዌር ኢንዱስትሪው እንደምታገኝ ጠቅሰዋል።

‎ኢትዮጰያም ያላትን የሰው ሀይል በኮደርስ በማሰልጠን፣ ከተወዳዳሪነት ባለፈ በዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ያስችላታል ብለዋል፡፡

‎እንደ ሀላፊው ገለፃ፣ ስልጠናው በአገር አቀፍ ደረጃ የቴክኖሎጂ ትራንስፎርሜሽን ለማሳካትና የነቃ ህብረተሰብ ለመፍጠር የሚያግዝ ነው፡፡

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review