አዲስ አዝማሚያ- የቅደመ መደበኛ ምረቃ ፕሮግራም የተጋነነ ወጪ

You are currently viewing አዲስ አዝማሚያ- የቅደመ መደበኛ ምረቃ ፕሮግራም የተጋነነ ወጪ

ቤተሰብ ለልጁ ደስታ በብዙ እንደሚጨነቅ ይታወቃል፡፡ አስተምሮ ትልቅ ደረጃ የማድረስ ዕቅድ የብዙ ቤተሰብ መሻት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ውስጥ ግን ገደብ ያለፉ እና አላስፈላጊ ወጪዎች ይስተዋላሉ፡፡ በተለይም ህጻናት ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ሲመረቁ የሚስተዋለው ከፍተኛ ወጪ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተጋነነ መጥቷል፡፡በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ኤ ኤም ኤን ዲጂታል የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራንን አነጋግሯል፡፡

የቅድመ መደበኛ ሕጻናት ምረቃ ላይ የተጋነነ ወጪ ማውጣት በቤተሰብ ላይ ጫናው እያየለ መምጣቱን በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሶሲዮሎጂ እና አንትሮፖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዘርሁን ዶዳ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

ቤተሰብ ለልጁ ደስታ ማንኛውንም መስዋዕትነት ይከፍላል ያሉት ዘርሁን (ዶ/ር) እንደ ወላጅ  የመጀመሪያ ፍላጎታችን ልጆቻችን ደስተኛ ሆነው ማየት ነው፡፡ የእድገት ደረጃቸውንም ማክበር እንፈልጋለን። ነገር ግን የሚደረገው ነገር ስለልጁ መሆኑ ቀርቶ ስለ ወላጆች ማህበራዊ ገጽታ መገንቢያ ሲሆን ግን ገደቡን ያልፋል ብለዋል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት ለቅድመ መደበኛ (ኬጂ) ምረቃ ፕሮግራም ሲሉ “ብድር ውስጥ በመግባት ከማን አንሼ በሚመስል አካሄድ የሚደረገው የትኛውም ከልክ ያለፈ ወጪ ጥበብ አይደለም። እንደዚህ ዓይነት ወጪ የቤተሰብን ኢኮኖሚ በመጉዳት የገንዘብ ጫና መፍጠር እንደሌለበትም ያነሳሉ፡፡

በሌላ በኩል የአምስት ዓመት እና የስድስት ዓመት ልጅ ደስታ የሚመነጨው ከቀላል ነገሮች ነው የሚሉት የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ፤ በአነስተኛ ወጪ ከኬክ ጀምሮ ከጥቂት ጓደኞች ጋር መጫወት፣ አዲስ አሻንጉሊት እና የወላጆቹን ሙሉ ትኩረት ማግኘት ናቸው። ትልቅ አዳራሽ መከራየት፣ ፎቶ አንሺ ባለሙያ መቅጠር እና በመቶዎች የሚቆጠሩ እንግዶችን መጥራት ለልጁ ከባድ እና ግራ የሚያጋባ ከመሆኑም በላይ፣ ከልጁ እውነተኛ ደስታ ይልቅ ወላጆች ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጥፉት ነገር ይሆናል ብለዋል።

ቤተሰብ ልጆቹ ስኬትን እና የቤተሰብ ፍቅርን ከፍ አድርገው እንዲመለከቱ ማስተማር አለበት፡፡ በእያንዳንዱ የህይወት እርምጃ ትልቅ ቁሳዊ ሽልማት ይገባሃል ማለት በልጆቹ ላይ ጫና መፍጠር መሆኑን ዘርሁን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ለሕጻናት የሚደረገው የትኛውም አይነት ድግስም ሆነ ስጦታ ከእድገት ደረጃው ጋር የተመጣጠነ መሆን አለበት። የቅድመ መደበኛ ምረቃ አስደናቂ እርምጃ ነው፣ ነገር ግን የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ አይደለም። ገደቡ ልከኝነትን ማወቅ እና ትኩረቱ የልጁን ትንሽና እውነተኛ ስኬት በማክበር ላይ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፤ ለሕዝብ እይታ ተብሎ የሚደረግ ትርዒት መሆን የለበትም ሲሉ ዘርሁን (ዶ/ር) ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

የተጋነነ የቅድመ መደበኛ ምረቃ ወጪ በልጆቹ ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?

የተጋነነ የቅድመ መደበኛ የምረቃ ወጪ በልጆቹ ላይ ተጽዕኖው ከምናስበው በላይ ውስብስብ ነው። በውጫዊ መልኩ፣ ለአንድ ቀን ህፃኑ እንደ ልዑል ወይም ልዕልት ሆኖ ሊሰማው እና በትኩረት መሃል በመሆኑ ሊደሰት ይችላል። ነገር ግን በስነ-ልቦናዊ ሁኔታ፣ የረጅም ጊዜ ውጤቶቹ አሉታዊ ሊሆኑ ይችላሉ።

ትልቅ ድግስ ለሚያደርግለት ቤተሰብ ልጁ የተዛባ እውነታን ሊፈጥርበት ይችላል። ስኬትን ከጠንካራ ሥራቸው እንደ መማር፣ ጓደኞች ማፍራት ጋር ሳይሆን ከድግሱ ግዝፈት ጋር ማያያዝ ሊጀምሩ ይችላሉ። ይህ ገና በለጋ ዕድሜያቸው የቁሳዊነት እና የተጋነነ የመብት ስሜት ዘርን ሊተክል ይችላል፡፡ ይህም ለወደፊቱ እያንዳንዱ ስኬታቸው ላይ ይህን የመሰለ ዝግጅት እንዲጠብቁ ያደርጋቸዋል፣ ይህ ደግሞ ዘላቂነት የለውም።

እነዚህን ድግሶች ለሚታደሙ ሌሎች ልጆች፣ ተጽዕኖው ፈጣን ሊሆን ይችላል። ወደ ቤታቸው ሄደው ወላጆቻቸውን ‘እኔ ለምን እንደዚህ ዓይነት ድግስ አልተደረገልኝም? እንደ እሱ/እሷ ያህል አትወዱኝም?’ ብለው ይጠይቃሉ። የበታችነት ስሜት እና ማህበራዊ ንጽጽር የሚጀምረው በዚህ መልኩ ነው። በእኩልነት አብረው መጫወትን በሚማሩበት ዕድሜ ላይ የቤተሰቦቻቸውን የገንዘብ ሁኔታ እንዲያወዳድሩ ይገደዳሉ። በጓደኞች መካከል መከፋፈልን እና ቅናትን ሊፈጥር ይችላል።

ስለዚህ ምንም እንኳን የአንድ ቀን ዝግጅት ቢመስልም በማህበራዊ መደብ እና በቁሳዊነት ላይ የሚሰጥ የመጀመሪያ ትምህርት ሆኖ ሊወሰድ ይችላል፤ ለማንኛውም ልጅ ግን ጤናማ አይደለም ሲሉ ዘርሁን (ዶ/ር) ተናግረዋል።

የቤተሰብ አማካሪና ኮንሳልታንት አቶ ብርሃኑ ራቦ በበኩላቸው የዘርሁን ዶባ (ዶ/ር) ሃሳብ ይጋራሉ፡፡  በባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ለህጻናቶች የሚደረገው የተጋነነ የምርቃት ስነስርዓት ሳይሮጡ እንዳሸነፉ፤ ሳይጀምሩ እንደጨረሱ ሳይወዳዱ ዋንጫ እንዳሸነፉ የማድረግ አዝማሚያ መሆኑኑ አንስተዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ አክለው ልጆቹን ከማንገላታት እና ከማድከም ባለፈ በልጆቹ የወደፊት ዕድገት ላይ የሚያመጣ  ለውጥ የለውም ባይ ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተግባራት ልጆቹ በልጅነት አዕምሯቸው መሸከም የማይገባቸውን ሸክም ማሸከም መሆን የቤተሰብ አማካሪው ተናግረዋል፡፡

ከመጠን ያለፈ ወጪ በማህበረሰቡ ላይ ምን ሊያስከትል ይችላል?

ማህበራዊ መዘዙ በጣም ጎጂ መሆኑን የጠቆሙት የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ የማህበራዊ ጫና ዑደትንም ይፈጥራል ባይ ናቸው። አንድ ቤተሰብ የተጋነነ ድግስ ሲያደርግ፣ ለማህበረሰቡ አዲስ ያልተፃፈ መስፈርት ያስቀምጣል። ቀጣዩ ቤተሰብ ይህንኑ ለማድረግ ወይም ለመብለጥ ይገደዳል፡፡ይህም ከልብ በመነጨ ፍላጎት ሳይሆን ሰዎች ምን ይሉኛል? ከሚል ፍራቻ የተነሳ ወይም ለልጃቸው ግድ እንደሌላቸው እንዳይታዩ በመስጋት አላስፈላጊ ወጪ ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ ነው።

መሰል አካሄዶች ለመካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል። ሰዎች ለአንድ ቀን ዝግጅት ሲሉ ለወደፊት ቁጠባ፣ ለሌሎች ወጪዎች እና ለወደፊት የትምህርት ቤት ክፍያ መዋል የነበረበትን ገንዘብ ያባክናሉ። ለቅድመ መደበኛ (ኬጂ) ምረቃ ብድር የሚወስዱ ሰዎች እንዳሉም ዘርሁን (ዶ/ር) ተናግረዋለ። ይህ አላስፈላጊ የገንዘብ ጫና ሲሆን የማህበረሰባችንን ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትንም ያዳክማል።

ይህ አዲስ አዝማሚያ የማህበረሰብ መንፈስን በግለሰባዊ ፉክክር ይተካል የሚል ስጋት እንዳላቸው ዘርሁን (ዶ/ር) ገልጸዋል። የልጆቻችንን የጋራ ስኬት ከማክበር ይልቅ፣ የግል ሀብትን የምናሳይበት መድረክ እያደረግነው ነው። ይህ የህብረተሰባችንን ትኩረት ከትምህርት እና ከማህበረሰብ እሴቶች ወደ ፍጆታ እና ማዕረግ እሴቶች ይቀይረዋል ሲሉ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ተናግረዋል።

በልጆች ላይ የስነ-ልቦና ጫና እንዳይፈጠር ምን ማድረግ አለበት?

ወላጆች አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር አለባቸው። ልጅ ደስታውን ከመቀበል ባለፈ የዝግጅቱን ትርጉም እንደገና መቅረጽ ያስፈልጋል። ለምሳሌ በጣም አስደሳች ድግስ ይመስላል! ከጓደኞችህ ጋር የተጫወትከው ምርጡ ጨዋታ የትኛው ነበር?’ ማለት ይችላሉ። ይህ ትኩረቱን ከድግሱ ግዝፈት ወደ ማህበራዊ ግንኙነት ይቀይረዋል።

ወላጆች የልጃቸውን ስኬት ትርጉም ባለው መንገድ ማክበር አለባቸው፡፡ ለልጆች የሚደረግ የትኛውም ነገር ከልጆች ጥረት ጋር ማገናኘት ያስፈልጋል። ጠንክረህ ስለሰራህ በጣም ኩራት ይሰማናል የሚሉ ማበረታቻ ቃላትን በመንገር ልጁ የሚከበረው በድግሱ ሳይሆን በራሱ ጥረት መሆኑን ያስተምረዋል።

አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው ለልጆች ደስታ የሚደረገው የትኛውም ነገር የወደፊት ህይወታቸውን የሚቀርጽ፤ ሩቅ አድርጎ የሚያሳይ እና ዓላማ እንድኖራቸው የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ ማንም ቤተሰብ  ለልጁ የፈለገውን ነገር የማድረግ መብት ቢኖረውም እጅግ የተጋነኑ ነገሮች ግን በህጻናቶች ላይ ስነ ልቦና ጫና ማሳደሩ አይቀረ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review