መላዉ ኢትዮጵያዊያን ሃምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተያዘዉን ሃገር አቀፍ እቅድ ለማሳከት ከማለዳዉ 12፡00 ጀምሮ እስከ ማምሻዉ 12፡00 ሰዓት ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች አሻራቸዉን ሲያኖሩ ዉለዋል፡፡
በሃገር ዉስጥ የሚገኙ ሚዲያዎችን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ ሚዲያዎች ይህንኑ በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር እንደወትሮዉ ሁሉ ዘንድሮም ተቀባብለዉ ዘግበዉታል፡፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካል የሆነውን በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር ማካሄዷን አሶሼትድ ኘረስ እና ኦል አፍሪካን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአንድ ቀን 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ሀገራዊ ዘመቻ ማድረጓን እና እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ 50 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል እየሰራች መሆኗንም በዘገባቸዉ ጠቅሰዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት፣ በ2011 ዓ.ም የተጀመረ እንደሆነ እና አላማውም ደንን መልሶ ማልማት ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑን ዘገባዎቹ ጠቁመዋል።
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ 40 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን እና በዚህ አመትም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱንም አስነብበዋል።
በብርሃኑ ወርቅነህ