ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ
በኮንስትራክሽን ግንባታ ዘርፍ እየተከናወኑ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል ግንባታቸው ወደ መጠናቀቁ የተቃረቡት የኢትዮጵያ ባህር ሀይል ጠቅላይ መምሪያ ቢሮ እና የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ቢሮዎች እንዲሁም የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተጎብኝተዋል።
የኢፌዲሪ መከላከያ ከለውጡ በኋላ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የቀጣዩን መከላከያ ዕድገት እና ዘመናዊነት ታሣቢ ባደረገ አግባብ በመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መገኘቱን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ተናግረዋል።
መከላከያ ለቀጣዩ ትውልድ በሚመች መልኩ የተሻለ እና ዘመኑን የዋጀ ተቋም ለማሥረከብ በሚፈለገው ልክ ጥራት እና ፍጥነት ፕሮጀክቶችን እየገነባ መገኘቱን ያነሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለተቋሙ የተመደበውን መደበኛ በጀት ያለ ምንም ብክነት በማብቃቃት ጥቅም ላይ በማዋል በርካታ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ መገንባት እየተቻለ ሥለመሆኑም አንስተዋል።
ከለውጡ በፊት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመተው ተቋም እና ሀገር ጎጅ ስራ ምክንያታዊነቱ የተመደበውን በጀት በአግባቡ ያለመጠቀምና ለብክነት መዳረግ እንደነበረም አውስተዋል።
አሁን ላይ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ መተው አይታሠብም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በየጊዜው ተቋማዊ ድጋፍና ክትትል በማድረግ በራስ አቅም በመደበኛ በጀት ከመቶ ያላነሱ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ እየተገነቡ ለአገልግሎት እየበቁ ሥለመሆናቸውም አንስተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ መከላከያ አዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ከመገንባት በዘለለ የነበሩትን ካምፖች እና የተቋሙን ልዩ ልዩ ማዕከላት በማደሥ እና በማሥፋፋት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል እያከናወነም ይገኛልም ነው ያሉት።
በ2018 በጀት ዓመት የተጀመሩትን መጨረስ እንደአሥፈላጊነቱ አዲስ መጀመር ያሚያሥችል ሥራ ላይ ትኩረት መሥጠት እንደሚገባ ያመላከቱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ጠቅላይ መምሪያ እና የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ቢሮዎች ጥራታቸውን በጠበቀ አግባብ ተገንብተው ወደ መጠናቀቁ መድረሳቸውን በጉብኝታቸው አረጋግጠዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በጎበኟቸው ሦስቱም ቦታዎች ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ ልማት አሻራቸውን ማኖራቸዉን የሃገር መከላከያ ሠራዊት ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል።