24/7 የሚሰራው የዓለማችን የመጀመሪያው ሮቦት

You are currently viewing 24/7 የሚሰራው የዓለማችን የመጀመሪያው ሮቦት

AMN- ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም

በቀን 24 ሰዓት፣ በሳምንት 7 ቀናት እና በዓመት 365 ቀናትን ሳያቋርጥ አገልግሎት የሚሰጥ ዎከር ኤስ 2 የተሰኘው ሮቦት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በቻይና ይፋ ተደርጓል፡፡

የቻይናው ዩቢ ቴክ ሮቦቲክስ የተባለው ሮቦት አምራች ኩባንያ የሠራው ኤስ 2 የተሰኘው ሮቦት በዓለም ዙሪያ በእጅጉ ተወዳጅነትን እያተረፈ ይገኛል፡፡

ሁለት ባትሪ የተገጠመለት ሮቦት አንደኛው ሃይሉን ሲጨርስ በ2ኛው ባትሪ ወዲያው እራሱን የሚተካ መሆኑ ነው በበርካቶች ዓይን ውስጥ እንዲገባ ያስቻለው ተብሏል፡፡

ሮቦቱ አገልግሎት መሥጠት ሳያቋርጥ ባትሪዎቹ ቦታ የሚቀያየሩ መሆናቸው ቀደም ሲል ከተሰሩት የባለ ሁለት እግር ሮቦቶች ልዩ ያደርገዋል፡፡

ባትሪዎቹ ኃይል እየጨረሱ መሆናቸውን ሮቦቱ ሲገነዘብ ደግሞ ወዲያው ወደ ባትሪ መለዋወጫ ጣቢያ በመሄድ በአዲስ ይተካውና ወደ ሥራው ይመለሳል፡፡

ኤስ 2 ሮቦትም ይህን ሲያደርግ የሚያሳይ ተንቀሰቃሽ ምስል በአምራቹ ድርጅት ተለቆ በስፋት ታይቷል፡፡

ባትሪ የመቀየር ሂደቱ ቀላልና በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሚከወን ሲሆን፣ ይህ ጊዜን የሚቆጥብ ቴክኖሎጂ በኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ አምራቾች ዘንድ መነቃቃት መፍጠሩን የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ያመለክታል፡፡

ሮቦቱ በተለይም ከፍተኛ የሰው ኃይል በሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎች፣ ፋብሪካዎች እና መጋዘኖች ውስጥ ለተከታታይ ሰዓታት እና ቀናት ሰውን ተክቶ ሊሠራ የሚችል መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review