የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራት የአጋር አካላት ሚናን የገመገመበትና በቀጣይ ለሚሠሩ ሥራዎች ግንኙነቱን የሚያጠናክርበት የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) አጋር አካላት የወረዳ ተሳታፊዎችን ከመለየት ጀምሮ በአጠቃላይ ለኮሚሽኑ ስራ ስኬት ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ለአዲስ ሚዲያ ኔት ዎርክ በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡
በውይይት መድረኩ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር)፣ አጠቃላይ የኮሚሽኑን የስራ ክንውኖች የተመለከተ ገለፃ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡
ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር)፣ በገለፃቸው በአጠቃላይ የምክክሩ ሂደት የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፣ በቀሪ የኮሚሽኑ ተግባራትም ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ከአጋር አካላት ጋር ቋሚ የውይይት መድረክ አለመዘርጋቱ፣ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት ወጥነት አለመኖር፣ በውይይቱ ላይ እንደ ክፍተት የተነሱ ጉዳዮች መሆናቸውንም ኮሚሽነር አምባዬ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡
እነዚህን ክፍተቶች በቀጣይ አርሞ የተቀናጀ ስራ መስራት የሚያስችል ከኮሚሽኑና ከአጋር አካላቱ የተውጣጣ አስተባባሪ ቡድን ተቋቁሟል፡፡
ቡድኑ በቀጣይ ከትግራይ ክልል እና ከዳያስፖራው ማህበረሰብ አጀንዳ ለማሰባሰብ በሚሰራው ስራ እንዲሁም በዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት ላይ ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እንዲሰራ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
በዛሬው የአጋር አካላት መድረክ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣ የእድሮች ጥምረት፣ የመምህራን ማህበር፣ ጀስቲስ ፎር ኦል፣ ደስትኒ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ኢንክሉሲቭ ዲሎጉ እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ተወካዮች መሳተፋቸውን መረጃው ያመለክታል፡፡