የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በካናዳ እና ሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዳያሰፖራ አባላት በአጀንዳ ማሰባሰብና በተሳታፊዎች መረጣ መርሐ-ግብር ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የዳያስፖራውን ማህበረሰብ የምክክር ሂደት ባለድርሻ አካል በማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ አጀንዳቸውን በመስጠት በአካል ተሳትፎ እንዲያደርጉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡
በመሆኑም በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ኮሚሽኑ በፈረንጆቹ ከነሐሴ 30 ቀን 2025 ጀምሮ በዋሽንግተን ዲሲ፤ እንዲሁም በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በፈረንጆቹ ከመስከረም 6 ቀን 2025 ጀምሮ በቶሮንቶ በሚያዘጋጀው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ ላይ እና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎችን በሚያስመርጥበት መርሐ-ግብር ላይ እንዲገኙ ጥሪ አቅርቧል።
ኮሚሽኑ በምክክር መድረኩ ላይ በግለሰብ ደረጃ ለመገኘት ለሚፈልጉ በኮሚሽኑ ፌስ ቡክ ገፅ ላይ መመዝገቢያ ሊንክ ማስቀመጡንም የገለፀ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ይገባል የሚሏቸውን አጀንዳዎች ይዘው በመገኘት በሂደቱ መሳተፍ እንደሚችሉ አስታውቋል።
የስብሰባውን ቦታ በመጪ ጊዜያት እንደሚያሳውቅም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡