አርብ ምሽት የተጀመረው የ2025/26 የውድድር ዓመት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ዛሬ ይከናወናል ።
ተከታታይ ዘጠኝ የውድድር ዓመት የመክፈቻ ጨዋታውን በኦልድትራፎርድ የሚያደርገው ማንችስተር ዩናይትድ አርሰናልን ያስተናግዳል ።
ዩናይትድ በተጠናቀቀው የ2024/25 የውድድር ዓመት በሊጉ ታሪክ አስከፊውን ውጤት አስመዝግቧል።
የ20 ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮን ከዚህ ዝቅታ ለመውጣት ሦስት ወሳኝ የማጥቃት ሚና የሚወጡ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።
ከ200 ሚሊየን ፓውንድ በላይ የወጣባቸው ማቴኡስ ኩኝሃ ፣ ብሪያን ምቤሞ እና ቤንጃሚን ሼሽኮ በሊጉ 44 ግብ ብቻ አስቆጥሮ 15ኛ ደረጃ ያጠናቀቀውን ክለብ ያሻሽላሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል ።
ቀያይ ሰይጣናቱ በመክፈቻ ጨዋታ ያላቸው ክብረወሰን ከየትኛውም ክለብ የተሻለ ነው ። ከ33 የፕሪሚየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ 22ቱን አሸንፈዋል ።
ማንችስተር ዩናይትድ ዘንድሮ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ከጨረሰ እንደ ስኬት ሊቆጠርለት ይችላል ።
ሦስት ተከታታይ የውድድር ዓመት ሁለተኛ ሆኖ ላጠናቀቀው አርሰናል ግን ዋንጫ ማንሳት እንደ ግዴታ ይቆጠራል።
መድፈኞቹ ከ22 ዓመት በኋላ የሊጉን ዋንጫ ለማሸነፍ ይረዱናል ያሏቸውን ተጫዋቾች አስፈርመዋል ።
በተለይ ቪክቶር ዮኬሬሽ እና ማርቲን ዙብሜንዲ የደጋፊውን ተስፋ ከፍ ያደረጉ ተጫዋቾች ናቸው።
ለአርሰናል የዘንድሮ የውድድር ዓመት 100ኛው ተከታታይ ተሳትፎው ነው ። በሊጉ ታሪክ ይህን የፈፀመ ሌላ ክለብ የለም ።
ይህን አስደናቂ ታሪካቸውንን በዋንጫ ለማጀብ ጉዞአቸውን በኦልድትራፎርድ ይጀምራሉ ።
መድፈኞቹ በኦልድትራፎርድ ያላቸው ክብረወሰን ግን የሚያኩራራ አይደለም ። ከ18 የመጨረሻ ጨዋታ በድል የተመለሱት በሁለቱ ብቻ ነው ። 10ጊዜ ተሸንፈው በስድስቱ አቻ ተለያይተዋል ።
ለአርሰናል ተስፋ የሚሰጣቸው ሁለቱ ድሎች የተመዘገቡት በአርቴታ ዘመን መሆኑ ነው ። የሰሜን ለንደኑ ክለብ ከሜዳው ውጪ ያለው ጥንካሬም ሌላ ተነሳሽነት ሊሰጠው ይችላል ።
የሚካኤል አርቴታው ቡድን በህዳር 2024 በኒውካስትል 1ለ0 ከተሸነፈ በኋላ ከሜዳ ውጪ ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች ሽንፈት አልተመዘገበበትም ።
ማንችስተር ዩናይትድ ከ አርሰናል እንደ ኦብታ ቁጥራዊ መረጃ 243 ጊዜ ተገናኝተዋል ። ዩናይትድ 99 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን አርሰናል በ89ኙ ድል ቀንቶታል ።
ማንችስተር ዩናይትድ ዛሬ ካሸነፈ አርሰናልን በ100 ጨዋታ የረታ የመጀመሪያው ክለብ ይሆናል ።
ምሽት 12:30 የሚጀምረው ተጠባቂውን ጨዋታ ሳይመን ሁፐር በዋና ዳኝነት ይመሩታል ።
በሸዋንግዛው ግርማ