የህዳሴው ግድብ ጎረቤት ሀገራትን በኃይል ያስተሳሰረ ነው

You are currently viewing የህዳሴው ግድብ ጎረቤት ሀገራትን በኃይል ያስተሳሰረ ነው

AMN- ነሐሴ 11/2017 ዓ.ም

ኢትዬጲያ የታላቁን ህዳሴ ግድብ መገንባቷ፣ ለጎረቤት ሀገራት ዘርፈ ብዙ ፊይዳ ያለው መሆኑን የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የጥናት እና ምርምር አማካሪ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና በጎረቤት ሀገራት አሁንም የኃይል ትስስሩ ያለ መሆኑን ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።

ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ቀደም ብለው በኃይል የተሳሰሩ ሀገሮች ሲሆኑ፣ በቀጣይም ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

ኢትዬጲያ በጎረቤት ሀገራት መካከል የሀይል ግንኙነት መፍጠሯ፣ በጎረቤት ሀገራት መካከል ያለው የቀጠናዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር አስተዋጽኦ ያለው መሆኑ ተመልክቷል።

ቀጠናዊ ትስስሩን የበለጠ ለማሳለጥ ከሚረዱ የልማት ዘርፎች እና የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እውን ለማድረግ ከተቀመጡ ግቦች አንዱ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ጎረቤት ሀገሮችን ማስተሳሰር የሚል መሆኑን አቶ ፈቅ አህመድ አብራርተዋል።

ጎረቤት ሀገሮች ንፁህ የኤሌክትሪክ ኃይል በተሻለ ዋጋ ማግኘታቸው፣ በሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሳድገዋል ሲሉ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የጥናት እና ምርምር አማካሪው ተናግረዋል።

በተጨማሪም በኤሌክትሪክ ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በቴክኒካል ትብብር እና በሌሎችም ዘርፎች የጠበቀ ግንኘነት እንዲኖር ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።

ከምንም በላይ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አቶ ፈቅ አህመድ ተናግረዋል።

በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት ካለ በጎረቤት ሀገራት መካከል የአላማ አንድነት ይፈጠራል ሲሉም አክለዋል።

ይህ የአላማ አንድነት ደግሞ ከሦስተኛ ወገን የሚመጣውን ያልተገባ ጫና በጋራ ለመቋቋም እንደሚያግዛቸውም ጭምር አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ወደፊት የምትገነባቸው በርካታ ግድቦች መኖራቸው፣ ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ተጨማሪ ኃይል የማግኘት ተስፋ ስለሚኖራቸው፣ የኢትዮጲያን የመልማት ፍላጎት የሚደግፋበት ሁኔታ ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አማካሪው ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ሁሉም ጎረቤት ሀገራት የራሳቸው የልማት ፕሮጀክቶች ያላቸው በመሆኑ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በግድቡ ዙሪያ ቀርበው የመስራት ፍላጎት ካላቸው፣ የራሳቸውን ግድብ እና ኃይል ማመንጫዎች ለመጀመር እንደ ፋና ወጊ ሆኖ ያገለግላቸዋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው ሲሉ ሙያዊ ትንታኔያቸውን አጋርተዋል።

በብርሃኑ ወርቅነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review