በነጩ ቤተመንግስት የተካሄደውን ውይይት ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለ40 ደቂቃ የዘለቀ የስልክ ንግግር አድርገዋል።
በስልክ ባደረጉት ንግግር በቀጣይ በሁለቱ መሪዎች መካከል የሁለትዮሽ ውይይት እንዲኖር ማመቻቸታቸውን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ገልፀዋል።
የተረጋጋ የተባለለት የነጩ ቤተመንግስት ውይይት ስኬታማ እንደበር በመሪዎቹ ተገልጿል።
ውይይቱ በጣም ጥሩ ነበር ያሉት ዘለንስኪ ለዩክሬን እጅግ አስፈላጊ በሆነው የደህንነት ዋስትና ላይም በስፋት መክረናል ብለዋል።
ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት ወደ ሰላም ስምምነት እንዲደርሱ ተኩስ አቁም ማድረግ አስፈላጊ አለመሆኑን ቢገልፁም ይህ ሀሳብ ከፈረንሳይና ጀርመን መሪዎች ተቃውሞ ገጥሞታል።
የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን እና የጀርመኑ ፍሬድሪክ መርዝ ተኩስ አቁም የግድ አስፈላጊ ነው ባይ ናቸው።
ውይይቱን ተከትሎሎ ለጋዜጠኞች ንግግር ያደረጉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳት ዘለንስኪ ሞቅ ያለ እና ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።
እንደ ከዚህ ቀደሙ መበሻሸቅ ያልነበረበት እና ዩክሬን የፀጥታ ዋስትና ለማግኘት ምቹ ዕድል የተፈጠረበት መሆኑን አንስተዋል።
በውውይቱ ከተገኙ የአውሮፓ መሪዎች ጋርም አንድ ገፅ ነበርን ያሉ ሲሆን ለመሪዎቹ ምስጋና አቅርበዋል።
የአውሮፓ መሪዎች በተለይም የዩክሬን የፀጥታ ዋስትና ጉዳይ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ የዩክሬንን ሰላም የሚጠብቁ የአውሮፓ ወታደሮችን በዩክሬን ምድር የማየት ፍላጎት እንዳላቸውም በውይይቱ ላይ አንፀባርቀዋል።
ቀንና ቦታው ባይታወቅም በቀጣይ ዘለንስኪ እና ፑቲን የሚያደርጉትን ውይይት ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው ነው።
በማሬ ቃጦ