ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለ አራቱ የመደመር ቅጾች ምን አሉ?

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለ አራቱ የመደመር ቅጾች ምን አሉ?

AMN ነሐሴ 14/2017

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያሰናዱት አራተኛው ቅጽ የመደመር መንግሥት መጽሐፍ በቀረበበት አግባብ ልክ በሀገርም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ፈር ቀዳጅ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መንግሥት መጽሐፍን አስመልክቶ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ስለ አራቱም ቅጾች ገለጻ አድርገዋል። በገለጻቸውም ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፡-

👉 የመጀመሪያው ቅጽ መደመር የሚለው መጽሐፍ፤ ለመደመር አጠቃላይ እሳቤ መሠረት የሚጥል ነው። የመደመር ጽንሰ ሐሳብ ንድፈ ሐሳባዊ መሠረቱ የተቀመጠው በመጀመሪያው ቅጽ ላይ ነው።

👉 የመጀመሪያው ቅጽ ከሚያነሳቸው ወሳኝ ጥያቄዎች መካከል፤ የሰው ልጅ ፍላጎት ምን ይመስላል፣ ፍላጎቱን ለማሟላት በምን መንገድ ነው ሊራመድ የሚገባው የሚሉት ይጠቀሳሉ። እነዚህን ከሰው ጋር በማስተሳሰር መጽሐፉ በዝርዝር ያነሳል።

👉 በተጨማሪም ራሱ መደመር እንደ እሳቤ ምን ማለት ነው? የሚለውን በብዙ መገለጫዎች ያመላክታል።

👉መደመር ዓለምን እንዴት ይመለከታል? ስለ ዓለም ያለው ምልከታ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው እና በዲፕሎማሲው ረገድ ምን ይመስላል? የሚለውም በመጀመሪዯው ቅጽ በዝርዝር አለ።

👉በአጠቃላይ ቅጽ አንድ (መደመር) ሀገራዊ ጉዳዮቹን በፍልስፍና መነጽር ያስቀመጠ ሐሳብ ነው። ፍልስፍናዊ በሆነ መንገድ ያሉትን ችግሮች የሚተነትን ለእነዚያ ችግሮችም መልስ የሚያመላክት ነው። እንደ መደመር ያለ እሳቤ ለኢትዮጵያ አስፈላጊነቱ ምን እንደሆነም በዝርዝር አንስቷል።

👉ሁለተኛው ቅጽ የሆነው የመደመር መንገድ የተነሱትን ጉዳዮች ደግሞ ሐሳብ፣ ታሪክ፣ ስትራቴጂ በሚሉ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ከፍሎ ማየት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

👉በመደመር መንገድ ለይተን ካስቀመጥናቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አንዱ በወቅቱ የገጠሙንን ችግሮች በአራት የከፈልንበት ነው። እነሱም የለውጡ ሂደት የመደፈቅ አደጋ ያጋጠመበት፣ የለውጡን ሂደት ጥገናዊ ማድረግ፣ ለውጡን የተቀበሉ በመምሰል ለመጥለፍ የሞከሩ እና ለውጡ ሐቀኛ ሆኖ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣ ማስቻል የሚሉት ናቸው።

👉በለውጡ ጊዜ የተከተልነውን መንገድ ሊቀለብሱ (ሊጠልፉ፣ ተሃድሷዊ በሆነ መንገድ ሊያስኬዱ) የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳሉ ገብቶን፤ ሊከተሉን በማይችሉት ፍጥነት ብንጓዝ አቅም እያነሳቸው እየተንጠባጠቡ ይሄዳሉ በሚል ይህን ሐሳብ የወል አድርገን ለውጡ አሸንፎ እንዲወጣ ያስቻሉ ንድፎች የተቀመሩበት ቅጽ ነው።

👉 የመደመር ትውልድ የተሰኘው ሦስተኛው ቅጽ ከፍ እያለ መጥቶ የመደመር ሐሳብ የትውልድ ሐሳብ እንዲሆን፣ ለኢትዮጵያዊ ትውልድ የምንመኘውን እና ለኢትዮጵያ ይበጃል ያልነው ሐሳብ የተመላከተበት ነው።

👉 ቅጽ ሦስት የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የሚባለውን ያለፉት 100 ዓመታት ታሪክ በአምስት ምድብ በመክፈል የበየነ መሆኑን እና ለዚህም የተጠኑ ባሕርያት መኖራቸውን ያነሳል። በዚህም መሠረት የመጀመሪያው ትውልድ ወግ አጥባቂ፣ ሁለተኛው ትውልድ ህልመኛ፣ ሦስተኛው ትውልድ ውል አልባ፣ አራተኛው ትውልድ ባይተዋር፣ አምስተኛው እና አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ የመደመር ትውልድ ተብለው ተበይነዋል።

👉ትውልዱ በመደመር እሳቤ እንዴት እንደሚታነጽ በቅጽ ሦስት ተቀምጧል። በተጨማሪም ስለ ጥበብ፣ ውበት፣ ‘ኢሞሽናል ኢንተለጀንስ’፣ ተፈጥሮን በመገንዘብ ተስማምቶ ስለመኖር በዚሁ ቅጽ ተብራርቷል።

👉 ብዙ ጊዜ መንግሥታት ያልደፈሩትና የመደመር ትውልድ ደፍሮ ካነሳቸው ሐሳቦች አንዱ የመካከለኛው ምሥራቅ እና ቀይ ባሕር ጉዳይ ነው። የቀይ ባሕር ጉዳይ ሰሞኑን የተነሳ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ።

👉 በአጠቃላይ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ከትውልዱ ምን ይጠበቃል?፣ ምን የቤት ሥራ አለበት?፣ ምን ቢከውን ነው የበለጸገች፣ የተሻለች ፣ የላቀች ኢትዮጵያን መፍጠር የሚችለው የሚለውን ሐሳብ የመደመር ትውልድ በዝርዝር ዳስሷል።

👉አሁን የተሰናዳው አራተኛው ቅጽ የመደመር መንግሥት ይባላል። በዘመናዊት ኢትዮጵያ ያሉ መንግሥታት የመንግሥታቸውን ቅርጽ፣ የመንግሥታቸውን እሳቤ፣ የመንግሥታቸውን አደራረግ በዚህ መንገድ ሠንደው አስቀምጠው አያውቁም።

👉 የመደመር መንግሥት አቀራረብ እና ዝግጅት በኢትዮጵያ ታይቶ አያውቅም። በአፍሪካ ደረጃም በእንደዚህ ዓይነት መልክ መንግሥታቸው ያለው እሳቤ፣ ያተገባበር ስልቱን፣ የሚከወንበትን መንገድ፣ ሊያሳካ የሚያስበውን ግብና ውጤት በዝርዝር ያስቀመጠ እና ለሕዝቡም የገለጸ መንግሥት የለም። ይህ በራሱ ፈር ቀዳጅ ያደርገዋል።

👉 የመደመር መንግሥት ዋና ሐሳቡ በጽንስ (በንድፍ) ያየነውን መደመር፣ በፍልስፍና ያየነውን መደመር፣ ታሪኩንና ጉዞውን ያየነውን መደመር፣ ትውልድን እንዴት እንደሚሠራ ያየነውን መደመር ተቋማዊ ቅርጽ እንዲይዝ ያደርገዋል።

👉መንግሥታዊ ቅርጽ እንዲይዝ የሚያደርገው ይህ ሠነድ ነው፤ ሐሳቡ ከግል፣ ከቡድን ወጥቶ እንደ መንግሥት እሳቤው እንዴት እንደሚተገበር በዝርዝር ያስቀምጣል።

👉 አንደኛ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚታየው ከዓለም ጋር የት ተላለፍን? እኛ እና የተቀረው ዓለም የተላለፍነው የት ነው? ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ስብራቶቻችን የት ጀመሩ? በሚል እኛን ከዓለም የለዩንን ነገሮች በዝርዝር ያነሳል።

👉ኋላ ለመቅረታችን ምክንያት የሆኑ ፈተናዎች፣ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? የሚሉትን በዝርዝር ያትታል።

👉በተጨማሪም በእኛ እና በዓለም መካከል የተፈጠረውን ክፍተት እንዴት ልናጠብበው እንችላለን? ምን ዓይነት መደመራዊ አካሄዶች ብንከተል ሊጠብብ እንደሚችል ይተነትናል።

👉ታሪኩን ካነሳ እና ክፍተቱን ከለየ በኋላ አይተውም፤ መጥበብ የሚችሉበትን መንገዶችም ያመላክታል። ያን ለማድረግ ከተለመደው የመቅዳት አካሄድ ተላቅቀን መደመራዊ ፈጠራ፣ መደመራዊ ፍጥነት እና መደመራዊ የዝላይ መንገዶችን መከተል አለብን። ካልፈጠርን፣ ካልፈጠንን፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ደግሞ ካልዘለልን በስተቀር ያንን ክፍተት ለማጥበብ እንቸገራለን ብሎ በዝርዝር ያትታል።

👉 ሐሳቡን ሲዘረዝር ከቀደሙ መንግሥታት ኃልዮቶች ጋር ራሱን ያወዳድራል። ለምሳሌ ገበያ መር ባልንበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ያወዳድራል። ወይም የዕዝ ኢኮኖሚ ባልንባቸው ወቅቶች የነበረውን አሠራርና አደራረግ ያወዳድራል። ልማታዊ መንግሥት ያልንባቸውን ጊዜያትም እንዲሁ። እነዚህን ኃልዮቶች በማንሳት በንጽጽር ያነሳል።

👉 በሁለተኛነት መደመርን ፍልስፍናው አድርጎ የሚመራ መንግሥት ምን ዓይነት ባሕርያት እንዳሉት በዝርዝር ያስቀምጣል። ስለሚከተለው ስትራቴጂ እንዲሁ በዝርዝር ያትታል። ስለሚያስመዘግበው ውጤት፣ ስለሚኖረው ግንኙነት፣ የዘመነ ገጠር፣ የተሳለጠ ከተማ እንዴት መፍጠር እንደሚቻል ያነሳል።

👉 ለስኬታችን ወሳኝ ጉዳዮችንም በሦስተኛነት ያነሳል። የፖለቲካ ስክነት ለኢኮኖሚ ስምረት የሉትን ጭምር።

👉 በሌላ በኩል ዕቅዶች እንዳይሳኩ የሚያደርጉ ተግዳሮቶችንም (ችግሮችን) ያነሳል። ድልብ ሐብቶችን እየመነዘርን የምንጠቀምበትን ሁኔታና የመፍትሔ ሐሳቦችን ያመላክታል። የጋራ ትርክት መገንባት፣ ሐሳብ ላይ የሚጫወት የፖለቲካ ምኅዳርን ማስፋት ላይም ያብራራል የሚሉትን እና ሌሎች ዋና ዋና ነጥቦችንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቃለ ምልልሳቸው ወቅት አንስተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review